ጋዳፊ – መለስ፤ መለስ – ጋዳፊ
በአፍሪቃ ምድር በየእለቱ ታሪክ እየተሰራ ነው!!!
የሊቢያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ንጉሠ ነገሥት ነኝ ባዩ “አፄ በጉልበቱ” የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊም ወንበር ተነቃንቋል። ጋዳፊ ለአርባ ሁለት ተከታታይ አመታት ሊቢያን ገዝቷል፤ በሊቢያ ሃብት ተንደላቋል፤ የመጣለትን እየተናገረ፤ ያሻውን እየፈፀመ ተጨማልቋል። እንኳንስ በሃገሩ በአፍሪካ ኅብረትም “ሃይ” የሚለው አጥቶ ተሞላቋል።
አሁን ግን እየመሸበት ነው። ሊቢያዊያን ደፍረው አምባነንነቱ ነግረውታል። “ልቀቅ፣ ውጣ፣ አንፈልግህም” ብለውታል። እንደ ቅዱስ ቁርዓን ሊታይ ትንሽ ቀርቶት የነበረው አረንጓዴ መጽሃፉ በአደባባይ ተቃጥሏል። በአረንጓዴ አደባባይም “ጋዳፊ ውረድ!!!” ተብሎ ተጭሆበታል። ከእንግዲህ ሊቢያ የቀድሞዋ ሊቢያ እንደማትሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ጋዳፊ በግብዝነትና ጭካኔ መለስን የሚመስል አምባገነን ነው። መለስ ገና ሚኒሊክ ቤተመንግስት ከመግባቱ በፊት ጀምሮ የጋዳፊ ወዳጅና አድናቂ እንደነበረ ይታወቃል። ራሱ ጋዳፊ ከመለስ ጋር ስለነበራቸው ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፉ የመለስ ሴራዎችና ተንኮሎችን በግዴለሽነቱ ይፋ አድርጓቸዋል። መለስና ጋዳፊ ተመሳሳይ እኩይ ባህሪያት ናቸው።
ዛሬ ጋዳፊ በራሱ ህዝብ ላይ እየፈጸማቸው ያሉ ተግባራት መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፈጽሟቸዋል። ለአብነት ያህልም የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
- ጋዳፊ በቀን አምስት መቶ ዶላር የሚከፈላቸው ቅጥር ነብሰ ገዳዮችን ከጎረቤት አገራት እያስመጣ በራሱ ህዝብ ላይ አሰማርቷል። እነዚህ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ህፃን፣ አዋቂ፤ ወንድ፣ ሴት ብለው ሳይመርጡ ሊቢያዊያንን በጠራራ ፀሃይ ጨፍጭፈዋል። መለስ ዜናዌም በተለያዩ ጊዜዓት ተመሳሳይ ተግባር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፈጽሟል። በተለይም በምርጫ 97 ማግሥት የሰለጠኑ ነብሰ ገዳዮችን በማሰማራት ህፃንና አዋቂን፤ ወንድና ሴትን ሳይለዩ በጭፍን ጨፍጭፈዋል። ልዩነቱ መለስ ነብሰ ገዳዮችን ከሌላ አገር ማስመጣት ሳያስፈልገው ከአገር ውስጥ መመልመል መቻሉ ብቻ ነው።
- ጋዳፊ የራሱን ህዝብ በጦር ሠራዊት አስደብድቧል። አልታዘዝ አሉት እንጂ ሰላማዊ ሰልፈኖችን በአይሮፕላን ለማስደብደብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። መለስ ዜናዊም በጦር ሠራዊት ህዝብን አስደብድቧል። በአይሮፕላንና ታንክ ሳይቀር ሰላማዊ ህዝብና መንደሮችን አውድሟል። ኦጋዴን፣ ጋምቤላና አዲስ አበባ ቋሚ ምስክሮች ናቸው። በዚህ ረገድ በጋዳፊና በመለስ መካከል ያለው ልዩነት ጋዳፊ ከልቡ “ህዝቤ” በሚለው ላይ የዘመተ ሲሆን መለስ ግን ከልቡ “ህዝቤ” የሚለው የሌለ መሆኑ ነው።
- ጋዳፊ ህዝብን በህዝብ ላይ አነሳስቶ ሊቢያውያን እርስ በእርስ እንዲጨፋጨፉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው። ደጋፊዎቹን “ አይጦችን አደባባይ ወጥታችሁ ግጠሟቸው” ሲል ይፋ ጥሪ አድርጓል። በዚህ ነጥብ መለስ ጋዳፊን በብዙ እጥፍ ይበልጠዋል። ጋዳፊ ይህንን ተግባር የፈፀመው በያዝነው ሳምንት ሲሆን መለስ ግን ይህንኑ ተግባር ባለፉት ሃያ ዓመታት በተከታታይ ሲፈጽመው የነበረ ጉዳይ ነው።
- ጋዳፊ የነፃነት ታጋዮችን “ወሮበሎች”፣ “ከሃዲዎች”፣ “አይጦች” እያለ ሰድቧቸዋል፤ አዋርዷቸዋል። መለስ የነፃነት ታጋዮችን “ከሃዲዎች”፣ “ፀረ-ሰላም ኃይሎች”፣ ፀረ-ልማት ኃይሎች”፣ “አደገኛ ቦዘኔዎች”፣ “ነፍጠኞች” እያለ ሰድቧቸዋል፤ አዋርዷቸዋል።
- ጋዳፊ ተቃውሞ ሲጠነክርበት ህዝብ መረጃ እንዳያገኝ አልጀዚራን አፈነ፤ ኢንተርኔትና ቴሌፎንን አወከ። መለስ ዜናዊ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በደነገጠ ቁጥር የሚያደርገው ነገር ነው። ጋዜጠኞችን ማዋከብ፤ የራድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶችን ማወክ የተለመደ ተግባሩ ነው። አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ የባልደረቦቹን ውድቀት እንዳይመለከት አልጀዚራን አፍኗል።
- የጋዳፊ የስልጣን ክር ቀጥና ልትበጠስ በደረሰችበት በአሁኑ ሰዓትም በቴሌቪዥን ባደረገው ንግግር ህዝብ በእሱ ጋር እንደሆነ፤ ሁሉም ነገር በቁጥጥሩ ሥር እንዳለ ቀባጥሯል፤ ተቃዋሚዎቹንም ዘልፏል። መለስ ዜናዊ ባለፉት ሃያ ዓመታት የኖረበት ሁኔታ የዚሁ ተመሳሳይ ነው። መለስ ከሃቅ ጋር አይተዋወቅም፤ የህዝብ ልብ የት እንዳለ አያውቅም፤ ትዕቢተኛ ነው፤ ሰዎችን መዝለፍ ብልህነት ይመስለዋል።
በቴሌቪዥ መስኮት ላይ ጠረጴዛ እየደበደበ ጮሆ በመናገር ጠንካራ መስሎ ለመታየት ቢሞክርም ጋዳፊ መውደቁ አይቀርም። ምናልባትም ይህ ርዕሰ አንቀስ ሳይታተም ሊወድቅ ይችል ይሆናል። አሊያም ጥቂት ቆይቶ ይወድቃል። የጋዳፊ አወዳደቅ ከቱኒዚያው ቤን ዓሊ እና ከግብጹ ሆስኒ ሙባረክ አወዳደቅ የከፋ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ከአሁኑ በሰብዓዊነት ላይ በሚደረግ ወንጀል እና በዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲከሰስ አቤቱታዎች ከያቅጣጫው እየተሰሙ ነው። መለስም መውደቁ አይቀርም። ጋዳፊ በሳምንት ጊዜ ውስጥ የሠራውን መለስ በአስርት ዓመታት ጊዜ ሠርቷልና የመለስ ውድቀት ከጋዳፊ ውድቀት የባሰ ይሆናል።
የጋዳፊን ውድቀት ለማየት ብዙ መጠበቅ እንደማያስፈልገን ሁሉ የመለስን አስከፊ ውድቀት ለማየት ብዙ መጠበቅ አያስፈልገን ይሆናል። እርግጥ ነው እንዲህ ዓይነቶቹን ነቀርሳዎች ለመገላገል ዋጋ መክፈል የማይቀር እዳ ነው።