የኦሮምያ ክልል መንግስት ለሰራተኞቹ ደሞዝ በጊዜ መክፈል እየተሳነው ነው ተባለ
በቂ ጥናት ሳይደረግባቸው ለፕሮፓጋንዳ እና ለዘረፋ እንዲመቹ ብቻ እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች የህዝብን ሃብት ለብክነት፣ እና ዜጎችን ለእንግልት እየዳረጉ ሲሆን፤ የኦሮምያ ክልል መንግስትንም እያዳከሙት ነው ስትል የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈችው ዘገባ ገልጻለች።
በአዳማ ከተማ የአባ ገዳ የስብሰባ አዳራሽ በአስርት የሚቆጠሩ የክልሉ የቢሮ ሃላፊዎች በተገኙበት ያለፉትን አምስት አመታት ሂደት የሚገመግም ስብሰባ እንደተካሄደ የገለጸችው ዘጋቢያችን፤ ከስብሰባው መሪዎች አንዱ ያለፈው የአምስት አመት እቅዳችን ምንም ፋይዳ አልነበረውም ብሎ ሲናገር መደመጡን እና ይህም ከተካፋዮቹ አንዱ የነበሩትን ምንጯን እንዳስገረመ ትናገራለች።
የዛሬ አምስት አመት በተካሄደው ስብሰባ ላይም መገኘታቸውን የሚገልጹት ግለሰብ፤ ዛሬ እቅዱ ምንም ፋይዳ እንደሌለው የሚናገሩት የክልሉ ባለስልጣናት፣ የዛሬ አምስት አመት የበላይ አዛዦቻቸው ሰው ሳያማክሩ በዘፈቀደ ፈጥረው የሰጧቸውን እቅድ ካላስፈጸማችሁ ብለው ያስገደዱን ናቸው ብለዋል። በክልሉ ውስጥ በቂ ጥናት ሳይካሄድባቸው በካቢኔው የዘፈቀደ ትእዛዝ ብቻ እየተካሄዱ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ከተፈጸሙ በኋላ አስቀድሞ ያልተገመተ ችግር በመፈጠሩ ከስራ ውጪ እንደሚሆኑ ለማወቅ ችለናል።
የክልሉን የገንዘብ አቅም ሳያገናዝቡ በየአቅጣጫው የተጀመሩት ስራዎችም የበጀት ጫና መፍጠር ጀምረዋል። እንደ ዘጋቢያችን ገለጻ፥ በአሁኑ ሰአት በክልሉ ከተሞች የሚሰሩ መምህራን እና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ደሞዛቸውን በጊዜ አያገኙም። ለህዝብ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተመለከተ፣ ለምሳሌ የቢሾፍቱ ከተማ ህዝብ የቧንቧ ውሃ ካገኘ አራት ወር ሊሆነው እንደሆነ ታውቋል።
የዘጋቢያችን ምንጭ፥ የክልሉን ቢሮዎች የስራ ሂደት ለማሻሻል በሚል ስም በስራ ላይ ውሎ አሁን ምንም ፋይዳ እንዳላስገኘ በሚነገርለት ቢ.ፒ.አር. ላይ ብቻ የባከነው ገንዘብ ለደሃው ህዝብ ሶስት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች ይገነባ ነበር ብለዋል።