የአዲስ አበባ ተማሪዎች በአገዛዙ ስለሚካሄድባቸው ግዳጆች ምሬት አሰሙ
የአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች፥ የወያኔ አገዛዝ በየጊዜው በሚያካሄደው ግዳጆች መሰላቸታቸውን በምሬት ለግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ገልጸዋል።
የወያኔ አገዛዝ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ህዝቡን በተለያየ ግዳጅ ወጥሮ መያዙ እና የደርግ ግዜን ትውስታ ማስነሳቱ ይታወቃል። ሰሞኑን፥ የአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ማእከላት በግዳጅ ተወስደው የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን እንዲያከብሩ ተደርገዋል።
የቦሌና የአካባቢው ተማሪዎች መገናኛ ወደሚገኝ የጎልማሶች ትምህርት ቤት የተወሰዱ ሲሆን፤ ደስተኞች እንዳልነበሩ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል። አንዳንዶቹ ተማሪዎች፥ በአሉ እውነት ለብሔር ብሔረሰቦች ክብር ነው ብለው እንደማያምኑ እና በአገዛዙ ቁጥጥር ስር ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የተቀናበረ የፕሮፓጋንዳ ዝግጅት መሆኑን ገልጸዋል። ወደማያምኑበት በአልም ተገድደው መምጣታቸው ደግሞ ተጨማሪ ንዴት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
የተማሪዎቹ ሁኔታ ወያኔ መልካም በማድረግ ሽፋን ስር ለመደበቅ የሚያደርጋቸው ሙከራዎች ሁሉ እየሰሩ እንዳልሆነ እና ህዝቡ የዘረኛውን አገዛዝ እውነተኛ ማንነት መረዳቱን ያሳያል ሲሉ አንድ አስተያየት ሰጪ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።