መለስን መፋረድ እንጂ መለማመጥ ቱርፋት የለውም

የኢትዮጵያ ቴሌኮሚውኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሰራተኞች ነን የሚሉ ሰዎች ባለፈው ሳምንት ጽፈው ለፍትህ ጋዜጣ ልከውታል በተባለ ደብዳቤ፣ ለዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ የሚገባውን ትችት ሰጥተውታል። “አንድ ጠብታ ፍሬ የማይወጣው ስብሰባ የሚሰበስብና የሚበትን”፣ “የህዝቦችን ጩኸት የሚያይበትና የሚያደምጥበት ግዜና ሞራላዊ ጥንካሬ የሌለው”፤ እና ‘’በሚቆጣጠረው ጦር ህዝቡን አፍኖ የሚገዛ አምባገነን’’ ብለውታል። በአገሪቱ ከተነሱት አምባገነኖች ውስጥ አንዱ እንደሆነም ነግረውታል።

ብቁ ባለሙያዎችን ከመንግስት ድርጅቶች እየገፋ አስወጥቶ በነሱ አባባል “እንኳን ስራቸውን እራሳቸውንም በማያውቁ” ካድሬዎች መሙላቱን፤ በዚህም ምክንያት በብዙ ቢሊዮን ብር የሚቆጠር ትርፍ የሚያስገኘው የህዝብ ኩባንያ መንኮታኮቱን ደብዳቤው አትቷል። ይኸም ሆኖ ግን ድርጅቱ ትርፋማነቱን እንዳላጣ፤ ነገር ግን ለዘረፋ እና ለብኩንነት የተጋለጠ እንደሆነም መስክረዋል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አፈና ከግምት በማስገባት፣ እንዲህ ያለ ደብዳቤ በገለልተኛ አካላት ምንም ሽረባ እና ተንኮል ከበስተጀርባው ሳይኖርበት በግልጽ መውጣቱ የሚያስገርም ነው። ይህ ጽሁፍ የድርጅቱን ሰራተኞች ለማጥመድ ያልተሸረበ ሴራ እና እውነተኛ ከሆነም ጸሃፊዎቹ ለድፍረታቸው ሊደነቁ ይገባቸዋል።

በርግጥ ዘረኛው አምባገነን መለስ እንዲህ አይነቱ ትችት ሲያንስበት ነው። “ሲያንስበት” ነው ስንል ቀልድ ይመስላል። መለስ ዜናዊን አሁን የሚገባው ትችት ሳይሆን ቅጣት ነው። ሁለት እጆቹ በጀርባው በኩል በብረት ካቴና ተከርችመው ፍርድ ፊት መቆም ይገባዋል። ላስገደላቸው ህጻናት እና እናቶች በህግ ፊት ዋጋ ሊከፍል ይገባዋል። የትችት ዘመን ካለፈ ሰነባብቷል።

ይልቅስ እኛን የገረመን፣ እንኳን እንደዚህ በቁጣ የሚጽፉ ይቅሩና፣ በትህትና የመከሩ ሳይቀሩ እስር ቤት በሚወርዱባት አገር እነዚህ “ኑሯችን ለአደጋ ተጋልጧል” የሚሉ ሰራተኞች ምሬታቸውን በግልጽ መግለጻቸው ነው። በርግጥም፥ ህዝቡ እየደረሰበት ስላለው መከራ መታገሱን እንዳቆመ እያሳዩ ካሉት ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው። ለቴሌ ሰራተኞች፣ ይበለው እንላለን።

ይሁን እንጂ አንድ ሳንጠቅሰው የማናልፈው ነጥብም አለ። የደብዳቤው ጸሃፊዎች፥ መለስ ዜናዊን ክፉኛ አውግዘው የህዝብ ጩኸት መስማት የማይችል አምባገነን መሆኑን ከነገሩት በኋላ፤ በድርጅታቸው ውስጥ ለሚካሄደው የተበላሸ አሰራርም በዋነኛነት ተጠያቂው እሱ መሆኑን ከጠቆሙ በኋላ፤ እሱው እራሱ መልሶ ከተጋፈጡት አደጋ እንዲያድናቸው ይማጸኑታል። ከሳጥናኤል የነፍስ ምህረትን እንደመለመን ሆኖ አግኝተነዋል።

መለስ ዜናዊ፥ የህዝብን ጩኸት እንዳይሰማ እና አገሪቱን እንደ ወንበዴ እንጂ እንደ ህዝብ አገልጋይ እንዳይመራ የሚከለክለው መሰረታዊ እንቅፋት አለበት። ይኸም፥ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ለባንዳ አድረው አገር ለመሸጥ ካልተሳካላቸው ቤተሰብ አብራክ የወጣ መሆኑና በትግራይ ተጋዳላይ ጉያ ውስጥ ተወሽቆ የመንግስትን በትረ ሥልጣን በጉልበት ለመቆጣጠር የበቃ ፣ ዘረኛ፣ ጸረ-አገር እና በጥላቻ የተሞላ ግለሰብ መሆኑ ነው። እንዲህ አይነት ጸረ አገር ስሜት በደም ሥሩ ውስጥ የተቀበረ ግለሰብ ደግሞ አገር ይከፋፍል፤ ይሰርቅ፣ ይዘርፍ፣ ይገድል እና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ያስር ይሆን እንጂ፤ አያንጽም፣ አይገነባም፣ መልካምን አያደርግም። እንደዛ የሚያደርግ መስሎ ቢታይ የቁጥጥር ዘመኑን ለማራዘም ሲል ጭንብል ለብሶ እንጂ ከልቡ አይደለም።

መለስ ዜናዊ በህዝብ የተፈጠረ እና ለህዝብ የቆመ መንግስት ቁንጮ ሳይሆን፤ በህገ-ወጥ መንገድ የሚገዛ የወንበዴዎች ቡድን መሪ ነው። እንዲህ ካለው ሰው ዘንድ ምህረትን መማጸን፣ ሰማይ ዝቅ እንዲል ፤ በሬ እንዲወልድ፤ ነጭ ጥቁር እንዲሆን፤ መመኘት ነው።

ታዲያ ለቴሌ ሰራተኞች የምንልከው ወንድማዊ ምክር፥ ነጻነታቸውን በነፈጋቸው፤ የሚገባቸውንም ከቀማቸው የወንበዴዎች ቁንጮ ፊት ወድቆ ፍትህን መለመን ትርጉም የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበው፤ ይህ ወንጀለኛ የሚጠይቁትን ቢሰጣቸው እንኳ ለማታለያ እና ለጊዜ መግዣነት የሚውል ጊዜያዊ መፍትሄ መሆኑን ተረድተው፤ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ትግል እንዲቀላቀሉ ነው። ዘር እና የፖለቲካ ታማኝነት ሳይሆኑ ብቃት እና ሙያ የዜጎችን የስራ ምድብ የሚወስኑባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚደረገውን ትግል እንዲያግዙ ነው። እንደ መለስ ዜናዊ ያሉትን የመከራቸውን አስኪያጆች ፍርድ ፊት ለማስቆም በሚደረገው ትግል እንዲሳተፉ ነው።