የትግራይ ገዢ ጉጅሌ የበላይነትን ማንገስ ከፌደራሊዝም ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም

ሰሞኑን በአንድ በኩል ረሃብና ችጋር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥጋብና ድግስ አዲስ አበባን እያናወጧት ነው። የትግራይ ገዥ ጉጅሌ በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ሁሉ ድግስ እያዘጋጀ ቢሆንም የአዲስ አበባው ግን ልዩ ነው። የየክልሉ ምስለኔዎችና ከአምስት መቶ በላይ የውጭ አገር እንግዶች ለዚህ ድግስ ተጋብዘዋል። የድግሱ መጠሪያ “የፌደራሊዝም ኮንፍረስ” ተብሏል።

የድግሱ መርሃ ግብር የሚከተለውን ይመስላል –

  • በቅድሚያ ነፃነታቸውን የተገፈፉ፤ በገዛ አገራቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ የሆኑ የኅበረተሰብ ክፍሎች በትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ምስለኔዎች መረገጣቸው የፈጠረላቸውን ደስታ ይገልፃሉ፤
  • ቀጥሎ መሬታቸው ተነጥቆ ለቱጃሮች የታደሉባቸው ገበሬዎችም ኑሯቸው ምን ያህል እንደተሻሻለ በዚሁ መድረክ ምስክርነት ይሰጣሉ፤
  • ቀጥሎ ደግሞ የአካዳሚ ነፃነት የተነፈጉ ምሁራን የአንድን ዘር የበላይነት ማስፈን እንዴት የህዝቦችን እኩልነት እንዳመጣ ይተነትናሉ፤
  • ከየክልሉ የመጡ ምስለኔዎች ደግሞ ወያኔ የፈለሰፈው ፌደራሊዝም ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ምትሃት የተላበሰ ስለመሆኑ ማስረጃዎችን ከየክልላቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እያጣቀሱ ያብራራሉ፤
  • ከእውነት እጅግ የራቁና የተጋነኑ የደስታ መግለጫዎች፣ የውሸት መረጃዎች እና የውሸት ዲስኩሮች ይደመጣሉ፤
  • በመጨረሻ ሮበርት ሙጋቤ፣ መለስ ከእሳቸው እሳቸው ደግሞ ከመለስ ስለተማሯቸው ጥበቦች በመናገር ድግሱን ይባርካሉ።

በዚህ ድግስ ብዙ ይበላል፤ ብዙ ይጠጣል። የብሄር ብሄረሰቦች የባህል ዘፈኖች በብዛት ይቀርባሉ። የእነዚህ ዘፈኖች መዘፈን የፊደራሊዝም ሥር መስደድ አመላካቾች ናቸው።

በልመና የሚተዳደሩ ድሆች ግን የድግሱ ተካፋዮች አይሆኑም። “ፊዴራሊዝም” በኢትዮጵያ ያመጣው እውነተኛ ውጤት ህያው ማስረጃዎች ናቸውና እንኳንስ እድግሱ ውስጥ በድግሱ ወቅት በከተማው ውስጥ እንዲገኙ አይፈቀድም። በዚህም ምክንያት ከሳምንት በፊት ተለቃቅመው ከከተማ ውጭ ተጥለዋል።

ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ዓይነቱን ውሸት ለሃያ ዓመታት ስንሰማ በመክረማችን ሰልችቶናል። ሃቁ የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ወርሮ የያዘውን አገር ከራሱ ብቻ በወጡ ሰዎች በሚመራ ሠራዊትና የስለላ ተቋም አማካይነት እየገዛ፤ ሃብቱን እየመዘበረ መሆኑ ነው። ይህንን የብዝበዛ ሥርዓትን ነው በየአካባቢው ለመለመላቸው ተላላኪዎቹ የይስሙላ ሹመት እየሰጠና የተጋጠ አጥንት እየጣለ “ፊደራሊዝም” እያለ የሚጠራው። ይባስ ብሎ በህዝብ ብዛትም ሆነ በመሬት ስፋት ከፍተኛው ድርሻ የያዙት የኅብረተሰብ ክፍሎች በይስሙላ ስልጣን ሳይቀር እየተገፉ አነስተኞቹ በብዙሃኑ ላይ የተሾሙበት ሥርዓትን ነው “ፌደራሊዝም” ብሎ የሚጠራው።

በተለያዩ የኅብረተሰባችን ክፍሎች መካከል ያለው ቅራኔ እጅግ አስጊ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሶ እየታየና ዘር ለይቶ መቧደን እና መቧቀስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ባህል እየሆነ መምጣቱ በግልጽ እየተስተዋለ የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ግን ስለብሄር ብሄረሰቦች መፋቀር መደስኮሩን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል።

ወያኔ በስሙ በሚነግድበት ሰፊው የትግራይ እና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ስር እየሰደደ የመጣው ቅራኔ አገራችን የት ያደርሳት ይሆን የሚለው ስጋት ከኢትዮጵያዊያን አልፎ የውጭ አገር ሰዎችን እያሳሰበ ባለበት ባሁኑ ወቅት ነው ወያኔ ስላስተሳሰራት ኢትዮጵያ መራቀቅ እነ መለስ ተክነውበታል።

የትግራይ ገዥ ጉጅሌ የጠፈጠፈው “ፌደራሊዝም” በማር የተለወሰ መርዝ መሆኑ ባለፉት ሃያ አመታት በተግባር ያየነው ጉዳይ ነው። የሆድ ጉዳይ ሆኖባቸው ነው እንጂ የገዥው ጉጅሌ ምስለኔዎችና ተላላኪዎችም ይህንን ያውቃሉ ብለን እናምናለን።

ወያኔና ፌደራሊዝም እሳትና ጭድ ናቸው። በዚህም ምክንያት ነው እውነተኛውን ፊደራሊዝም ለመከላከል የውሸት ፊደራሊዝም ገንብቶ፤ እኩልነትን እረግጦ፣ ነፃነታችን ገፍፎ፤ ሃብታችንን እየመዘበረ የሚሳለቅብን። በአጭር ጊዜ ውስጥ የትግራዩን ገዢ ጉጅሌ ከሥልጣን ካላባረርን የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ከ15 ዓመታት በፊት የተገላገሉት የአፓርታይድ ፌደራሊዝም ለልጆቻችንና ለመጪው ትውልድ ማውረሳችን የማይቀር ነው።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለነፃነትና ለፍትህ የምናደረገው ትግል አንዱ ግብ የትግራይ ገዢ ጉጅሌ የቀመመልንን መርዘኛና ዘረኛ ፌደራሊዝምን ማስወገድ እና በምትኩም በእኩልነት ላይ የተገነባ ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ሥራ ላይ ማዋል መሆኑን ተገንዝበን ትግላችን እናፋፍም ይላል። በፌደራሊዝም ስም ዘረኝነትን ማስፋፋትና አንድ ዘር የሌሎች የበላይነት ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የመግታት ኃላፊነት የኛ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!