በወያኔ አገዛዝ ላይ ሂስ እየተሰነዘረ ነው
ወያኔ አገዛዝ ፍራንስ ቴሌኮም የተባለ የውጭ ኩባንያ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽንን ለሁለት አመታት እንዲያስተዳድር መቅጠሩን ተከትሎ ሂስ እየተሰነዘረበት ነው።
አገዛዙ በ30 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ከ656 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፍራንስ ቴሌኮም ቴሌን እንዲያስተዳድርለት መቅጠሩ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።
ዶ/ር ዋልተንጉስ ዳርጌ የተባሉ እና በጀርመን አገር ፕሮፌሰር የሆኑ ኢትዮጵያዊ ባወጡት ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽን ከውጭ በመጡ ሰራተኞች እና ኩባንያዎች አገልግሎት ላይ ለመመርኮዝ የተገደደው ሊታደጉት የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ስለጠፉ አይደለም ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ፥ ከግንኙነት ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ልምድ ያላቸው እና በጀርመን አገር በዚሁ ዘርፍ አስተማሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የዶክተሬት ተማሪዎችን እንዲያስተምሩ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዘው ነበር። ይህንን ልምዳቸውን በስራ ላይ በማዋል አገራቸውን ለመጥቀም እንደሚፈልጉ እና ኮርፖሬሽኑ ባቀዳቸው ተግባራት ሊረዱ እንደሚፈልጉ አሁን የኮሚኒውኬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለሆነው እና በወቅቱ የቴሌ ቦርድ ሃላፊ ለነበረው ደብረጽዮን ገብረማሪያም ፍላጎታቸውን ማሳወቃቸውንም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ ጥሪያቸውን ችላ በማለት ከአንድ አመት በላይ ለጥያቄያቸው መልስ አለመስጠቱን በጽሁፋቸው አስፍረዋል።
የኢትዮጵያውያን ምሁራንን እገዛ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው ኮርፖሬሽን፣ በዘርፉ እውቀትና ልምድ ለሌላቸው ቻይናውያን አማካሪ ተብዬዎች ግን በአስር ሺሆች የሚቆጠር ደሞዝ ይከፍል እንደነበረም አጋልጠዋል። ለዝግጅት ክፍላችን መልክት ያደረሱ ሌላ ኢትዮጵያዊ፣ ወያኔ የአገሪቱን የሰው ሃይል ክፉኛ እያባከነ እንደሆነና፤ ቀደምት መንግስታት እንኳ ባቅማቸው ያካሄዱትን የአቅም ግንባታ ስራ እያፈራረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በቴሌ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ የሚታይ ችግር እንደሆነ ያስታወሱት ግለሰብ፤ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ስደት አገራቸውን ጥለው ለመውጣት በመገደዳቸው በአሜሪካ እና በአውሮፓ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያስተምሩ፤ ብቃት የሌላቸው የባዳ አገር ምሁራን ከፍተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችንን ሞልተውታል ብለዋል።