አዲስ ፍቅር ይዞኛል – የማደርገዉ ጠፍቶኛል!
አዎ! “አዲስ ፍቅር እኔን ይዞኛል – የማደርገዉ ሁሉ ጠፍቶኛል” – ቆየት ካሉት የብዙዬ በቀለ ዘመን አይሽሬ ዜማዎች አንዱ ነበር። ብዙዬ ይህንን ጣፋጭ ዜማ የተጫተችዉ አፍላ የወጣትነት ፍቅር እንዴት እንደሚያከንፍና መድረሻ እንደሚያሳጣ ልትነግረን ነበር። ዛሬ ከወደ አዲስ አበባ የሚሰማዉ የአዲስ ፍቅር ይዞኛል ዜማ ግን ብዙዬ ከተጫወተችዉ ጣፋጭ ዜማ እጅግ የተለየ ነዉ። ቅንጅቱና ዜማዉ ስሜት አይኮረኩርም፤ መዐዛዉ አይጣፍጥም፤ የዜማዉ አዝማሪና ድምፁ ሰዉ ሰዉ አይሸቱም። ይህ መለስ ዜናዊ በክራር ሳይሆን በክላሽንኮቭ በተወዛዋዥ ሳይሆን በአግአዚ ታጅቦ የሚጫወተዉ አዲስ ዜማ የሚነግረን የወያኔዉ ቁንጮ እጅግ ከሚጠላት ኢትዮጵያችን ጋር ድንገተኛ ፍቅር እንደያዘዉ ነዉ። አዎ! ድንገተኛ ፍቅር፤ አዲስ ፍቅር ወይም ያ” እፍ እፍ እያልን የምንጠራዉ የልጅነት ፍቅር መለስ ዜናዊን በስተርጅና ያዘዉ! መለስ ዜናዊ እንደ ስራዉ ምኞቱም አሰቀያሚ ካልሆነ በቀር ዛሬ በስተርጅናዉ እንዴት እድሜ ልኩን ካቆሸሻት፤ከጨፈለቃትና ታሪኳን ካንቋሸሸ አገር ጋር ፍቅር እንደጀመረዉ ሊገባን አልቻለም። ሆኖም ከሰሞኑ እንዳየነዉና እንደሰማነዉ እዉነትም ፍቅር እንደያዘዉ ሰዉ የሚይዘዉና የሚለቀዉን አሳጥቶታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣና አመፅ እያየለ መምጣት ስላሰጋዉ እሱ እራሱ ለፈጠረዉ የአገር ዉስጥ ችግር መፍትሄ ፍለጋ ከአገር ዉጭ መመልከት ጀምሯል።
ዛሬ በመረጃ ዘመን የሚኖሩ መንግስታትም ሆኑ የጥንቶቹ መንግስታት አገራቸዉ ዉስጥ በየቦታዉ የሚፈነዳዉን ህዝባዊ አመፅ በኃይል መግታት ሲሳናቸዉ ትኩረታቸዉን ወደ ዉጭዉ አለም ማድረጋቸዉ የተለመደ ነዉ። ጨቋኝና አፋኝ መንግስታት የራሳቸዉ ጎታች ፖለሲ የወለደዉን ህዝባዊ አመፅ ከቁጥጥራቸዉ ስር ለማድረግ የሚወስዱት የመጀመሪያ እርምጃ ኃይል መጠቀም ነዉ – ይህም ድብደባ፤ግድያ፤እስርና ስደትን ያጠቃልላል። ይህ ሁሉ አልሰራ ብሎ ህዝባዊ አመፁ የሚቀጥል መስሎ ከታያቸዉ ደግሞ የህዝብን ቁጣ ገለል የሚያደርግላቸዉ ሰበብ ይፈልጋሉ። ከነዚህ ሰንካላ ማዘናግያ ሰበቦች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ጦርነት ማወጅ ወይም ብሔራዊ ቀዉስ የሚፈጥሩ አተካራዎችን ሆን ብለዉ በመቀስቀስ ህዝብን ባንዲራና ብሔራዊ ጥቅም በሚሉ ቀስቃሽ መፈክሮች ዙሪያ ማሰባሰብ ነዉ። የዚህ ሤራ ሁነኛ ምክንያት ደግሞ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ሳይሆን አገር ዉስጥ አላስቆም አላስቀምጥ ያላቸዉን ህዝባዊ አመፅ ለማብረድና የሚበድሉትን ህዝብ ለእኩይ አላማቸዉ ለማሰለፍ ነዉ። ይህ አምባገነኖች በመጨረሻዉ ሰአት የሚወስዱት ቀቢፀ ተስፋ እርምጃ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደጋጋሚ የታየ ነዉና ለኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ የሚሆን አይመስለንም። ለምሳሌ ኮሎኔል መንግስቱ 17 አመት ሙሉ ያሰሩትንና የረገጡትን ህዝብ በመጨረሻ ሰአት ላይ “አገርህን ከመበታተን አድን” በሚል መፈክር ዙሪያ ለማስተባበር መሞከራቸዉ የሚዘነጋ አይደለም።
ህዝባዊ ቁጣን ለማብረድና ህዝብን ከተነሳሳበት ዋነኛ አላማ ለማዘናጋት ሲሉ ብቻ አለም አቀፍ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ገዢ መደቦች ከታረክ አለመማራቸዉ ብቻ ሳይሆን እራሳቸዉ በእማኝነት የታዘቧቸዉን ገጠመኞችም ቢሆን የማያስተዉሉ ልበ ቢሶች ናቸዉ። እዚህ ላይ አንድ ጎልቶ የሚታይ እዉነት ቢኖር ገዢ መደቦች ሆን ብለዉ የቀሰቀሱትን የማዘናግያ ጦርነት በድል ቢወጡም እንኳን ህዝብ ጀርባ ላይ የጫኑትን ጫና እስካላወረዱና የህዝብን መብትና ነፃነት እስካላከበሩ ድረስ ያ’’ ገድበዉ ያቆሙት የመሰላቸዉ ህዝባዊ አመፅ እያደር ይጠናከራል እንጂ ከድል በፊት አይቆምም። በተለይ ኢትዮጵያን በመሰለ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ በሆኑበት አገር መንግስት ያሻዉን ያክል የዉጭም ሆነ የአገር ዉስጥ ማዘናግያዎችን ቢፈጥር ህዝባዊ ቁጣዉና አመፁ ኃይል እያገኘ ይሄዳል እንጂ በፍፁም አይቀዘቅዝም። በገዛ አገሩ ዉስጥ እንደ ባሪያ መገዛት መርሮት የተነሳሳን ህዝብ ባንዲራና ብሄራዊ ጥቅም እያሉ ለማዘናጋት መሞከር ምግብ የራበዉን ህፃን ልጅ በሰርከስ ከመደለል የተለየ አይደለም። ታዳጊ ህፃናት ምንም ያህል ቢርባቸዉና ቢጠማቸዉ የሰርከስ ስም ሲነሳ ለግዜዉም ቢሆን ፊታቸዉ ይፈካል። ታድያ እነዚህን ህፃናት ሰርከስ ብንወስዳቸዉም የሰርከሱ ዝግጅት ካለቀ በኋላ ራበን ብለዉ አንደገና ማልቀሳቸዉ አይቀርም። ሰርከስ የራበዉን ህፃን ሆድ እንደማይሞላ ሁሉ ለህዝብ ችግር መሰረታዊ መልስ የማይሰጥ ግዜያዊ ድለላም የህዝብን አመፅ ማቆም አይችልም።
አገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ሺ ዘመን የታሪክ ቆይታዋ ከጎረቤቶቿ ጋር ተከባብራ በሠላም የኖረች አገር ብትሆንም ወንዞቿ፤ለምለም አፈሯና ስትራቴጂክ አቀማመጧ ያቋመጣቸዉ አንዳንድ አገሮች ጡንቻቸዉ የፈረጠመ በመሰላቸዉ ቁጥር ቢቻል ሊገነጣጥሏት አለዚያም ትላልቅ ወንዞቿንና ለምለም መሬቷን ለመቆጣጠር ያላደረጉት ጥረት የለም። ባለፉት አንድ መቶ አመታት እነዚህ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በቀጥታ ባይወጉንም ወኪሎቻቸዉን በመላክ ኢትዮጵያ ደካማና የተበታተነች አገር ሆና እንድትኖር ያልፈነቀሉት ድንጋይና ያልሸረቡት ሤራ የለም። ለአገራችን ለኢትዮጵያ ደንታ የሌላቸዉ የወያኔ መሪዎችም ቢሆኑ የዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ ዉጤቶች ናቸዉ።
ዛሬ እቺን መጣጥፍ ይዘንላችሁ እንድንቅረብ የገፋፋን ከሰሞኑ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ “ሀሁ” የቆጠረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሚገባ የሚያዉቀዉን የግብፅን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ጉዳይ ነዉ። ምክንያቱ ለየብቻ ቢሆንም ጋዜጣዊ መግለጫዉ እኛንም ግብፆችንም አስገርሟል። ወደ መለስ ዜናዊ ጉድ ከመግባታችን በፊት የኢትዮጵያና የግብፅ መንግስታትም ሆኑ የሁለቱ አገሮች ህዝቦች ካለምንም ዉጣ ዉረድ ሊቀበሉት የሚገባ አንድ ታሪካዊና የተፈጥሮ እዉነት አለ። ኢትዮጵያና ግብፅ የአባይ ወንዝ በተፈጥሮ ያስተሳሰራቸዉ አገሮች ናቸዉ። ምንም እንኳ ቅኝ ገዥዎች ዕዳው ለትውልድ የሚተላለፍ ኢሚዛናዊ የሆነ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ውል ተክለው መሄዳቸው በኢትዮጵያ መንግሥታት ዘንድ ለዘመናት ቅሬታ ሲያስነሳ የኖረ ጉዳይ መሆኑ ባይካድም የመለስ ዜናዊ ከ20 አመታት የቤተመንግሥት ቆይታ ቦኋላ ችግሩን እንደ አዲስ አንስቶ ርካሽ የፖለቲካ ድጋፍ ማግኛ ለማድረግ መሞከር አንኳን መለስ ዜናዊን በጸረ ኢትዮጵያዊነቱ ለምናውቀው ለኛ ለባለቤቶቹ ይቅርና በአንድ ወቅት የወያኔ ጉድፈቻ አባት ለሆኑት ግብጾችም ጭምር የማይዋጥላቸው ሆኖአል። ከሱዳን ጋር የሚያዋስነንን ከ1600 ኪሎመትር በላይ ለም መሬታችንን አሳልፎ የሰጠ ባንዳ፤ ድንግል እና ዜጎች ከአያት ቅም አያታቸው ጀምሮ የኖሩበትን ለም መሬት ነጥቆ ለባዕዳን በርካሽ ዋጋ እየቸበቸበ ያለ ማፊያ ቡድን አባይን ለማልማት ዕቅድ እንዳለው መስሎ ጠብ ያለሽ በዳቦ ጨዋታ ቢጀምር አላማው ምን እንደሆነ ከቶ አይረሳንም ።
ሌላዉ የሰሞኑ የኢትዮጵያዉያን የመነጋጋሪያ ርዕስ ሆኖ የሰነበተዉ መለስ ዜናዊ ግብፅ የኢትዮጵያን አማፅያን ትረዳለች ብሎ የተናገረዉ ዜና ነበር። ለመሆኑ እነዚህ አማፅያን እነማን ናቸዉ? ያሳመፃቸዉስ ምንድነዉ? መለስ ዜናዊ ይህንን የአማፅያን ጉዳይ ሐላፊነት ከጎደለዉ ከራሱ አስተዳደር አላቅቆ ከግብፅ ጋር ከማያያዙ በፊት እነዚህን አማፅያን ምንድነዉ ያሳመፃቸዉ ብሎ እራሱን መጠየቅ ነበረበት። መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዘረጉት የኤኮኖሚና የፖለቲካ ስርአት የዉጭ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ እንጂ ኢትዮጵያዉያንን የሚያስተባብር ስርአት አይደለም፤ ስለሆነም በአገራቸዉ በኢትዮጵያ ጉዳይ አያገባችሁም የተባሉ ኢትዮጵያዉያን የሚወዷት አገራቸዉ ከድጡ ወደ ማጡ ስትወርድ ዝም ብለዉ መመልከት በፍጹም አይችሉም። በአንድ ወቅት እሱ እራሱ አማፂ የነበረዉ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ በቅርቃር ቀርቅሮ የኔ ብቻ ነዉ ሲል በሩ የተዘጋባቸዉ አገር ወዳድ ዜጎች ሁሉ የተዘጋዉን ለማስከፈት ማመፃቸዉ አይቀርምና መለስ ዜናዊ ይህንን እሱ እራሱ የፈጠረዉን ችግር በሌሎች ላይ ማላከክ የሚኖርበት አይመስለንም።
ዛሬ ኢትዮጵያን የሚያምሳት ችግር አገር ዉስጥ እነ መለስ ዜናዊ የፈጠሩት ችግር ነዉ እንጂ ከዉጭ የመጣ ችግር አይደለም። መለስና ጥቂት ግብረ አበሮቹ የፈጠሩትን ይህንን ችግር ለመፍታት በአንድ ወቅት ኢትዮጵያዊያኖች አገራቸውን ከውጭ ወረራ ለመከላከል የፈጸሙትን ገድል የአንድ ትምክህተኛ ገድል አድርጎ ሲያንቋሽሽና ሲያጥላላ እንዳልነበረ፤ ከጊዜ ወደጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን ህዝባዊ ቁጣ ለማድበስበስ በህልውናችን ላይ የመጣ የውጭ ጠላት ያለ ይመስል የህዝባችንን የአገር ፍቅር ስሜት ለመኮርኮር እየተደረገ ያለው ቅስቀሳ ለምን አላማ እንደሆነ ይገባናል ። እድሜ ልካቸውን የኢትዮጵያችንን ታሪክ ሲክዱና ሲያናንቁ የኖሩት የመለስ አይነቶቹ ባንዳዎች የማያውቁት ነገር ቢኖር አገራችን ኢትዮጵያ ለውጪ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች የተጋለጠችባቸዉ ግዜያቶች ሁሉ አንደዛሬው ዘመን በትናንሽ ግጭቶች ምክንያት በአገር ዉስጥ ተከፋፍለን በነበርንባቸዉ ግዜያቶች ነበሩ። ለመከፋፈላችን ደግሞ ዛሬም ሆነ ትናንት ተጠያቂዉ ህዝብ ሳይሆን ከትናንሽ የስልጣን ጥቅም አሳልፈው ማሰብ የተሳናቸው መሪ ተብዬዎች ናቸው ። የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና የህዝቦቿ ህብረት እንደ ብረት የሚጠነክረዉም ሆነ እንደ ፈቱት ገመድ የሚላላዉ የኢትዮጵያ መንግስት አገር ዉስጥ የሚከተላቸዉን ፖሊሲዎች እየተከተለ ነዉ እንጂ ከዉጭ በሚመጣ ጫና አይደለም። ይህንን ስንል ደግሞ ኢትዮጵያ ጠላት የላትም ወይም እድገታችን ፤ህብረታችንና አንድነታችን ከባዕዳን ተፅዕኖ የፀዳ ነዉ ለማለት አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ምን ግዜም ቢሆን ጠላቶቿ ተኝተዉላት አያዉቁም ሆኖም እጃቸዉን ለመሰንዘር ድፍረት የሚያገኙት የአገር ዉስጥ ህብረታችን ላልቶ ሲያዩት ብቻ ነዉ። እዚህ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አበክሮ ሊገነዘበዉ የሚገባ ሁለት ቅርፅ ያለዉ አንድ እዉነት አለ፤ በአንድ በኩል የሚለያዩንን የአገር ዉስጥ ችግሮች በጋራ እስካልፈታናቸዉ ድረስ ከዉጭ የሚቃጣብንን አደጋ በጋራ መቋቋም አንችልም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዉያን እኩለነታችን፤መብታችንንና ነፃነታችን ሲከበር ማንኛዉንም የወጭ ጠላት መመከት መቻላችን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችንም ያዉቁናልና አይደፍሩንም። አገራችን ኢትዮጵያ በሰላሙ ጊዜ ጥቂቶች እንዳሻቸዉ የሚፈነጥዙባት በችግር ቀን ደግሞ ብዙኃኑ አገራቸዉን ከወራሪዎች ለማዳን ብቻ የሚፈለጉባት አገር አስከሆነች ድረስ ችግራችን ከዉጭም ከዉስጥም ማለቂያ አይኖረዉም።
መለስ ዜናዊ “ባንዲራችንን” ስንል ጨርቅ ነዉ ብሎ የተሳለቀ፤ ታሪካችንን ስንል “የአክሱም ሐዉልት ለወላይታ ምኑ ነዉ ብሎ የቀለደብንና፤ የ3000 ሺ ዘመን ታሪካችንን በአያቱ እድሜ ለክቶ ከአንድ መቶ አመት አይበልጥም ብሎ አፉን ሞልቶ የተናገረ ከሀዲ ሰዉ ነዉ። ይሀ ከሀዲ ግለሰብ “ኢትዮጵያዊነትን” ቢቻል ለማጥፋት አለዚያም ለማደብዘዝ 20 አመት ሙሉ ሽንጡን ገትሮ የታገለ የለየለት የኢትዮጵያ አንድነት ጠላት ነዉ። ታዲያ ዛሬ በነገሰ በሃያ አመቱ ምን ቢታየዉ ነዉ ለዚያ ሲያፈርሰዉ ለከረመዉ “ኢትዮጵያዊነት” ቁጥር አንድ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት የሚሞክረዉ? “ኢትዮጵያዊነት” ሳይጠፋና ሳይደበዝዝ እስከዛሬ የቆየዉ መለስ ዜናዊ ሳይሞክረዉ ቀርቶ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን እንደወለደዉ ልጅ በጉያዉ አቅፎ ስለተንከባከበዉ ብቻ ነዉ።
እዚህ ላይ መለስ ዜናዊን በተመለከተ ሁለት ነገሮችን አስተዉሎ መመልከት የግድ ይሆናል። በአንድ በኩል መለስ ዜናዊ 20 አመት ሙሉ ኢትዮጵያን ሲገዛ ወርቃማነቱን ነዉ ደጋግሞ የነገረን እንጂ አፉን አዳልጦት እንኳን ኢትዮጵያዊነቱን ነግሮን አያዉቅም። ጭራሽ ከሱ በፊት የነበሩት መሪዎች ያስለመዱንን አገሬ፤የአገሬ ህዝብ፤ህዝባችንና እናት አገር የሚባሉትን ቃላት መለስ ዜናዊ የሚያዉቃቸዉም አይመስልም። በሌላ በኩል ደግሞ መለስ ዜናዊ “ብሔር ብሔረሰቦች” ፤ “ፌዴራሊዝም”፤”ዲሞክራሲ”፤ እድገትና ልማት አሁን ደግሞ የትራንስፎርሜሺን ፕላን እያለ ህዝብን ሲያታልል ከርሟል; ከአሁን በኋላ ግን ይህ ዘረኛ ግለሰብ እንደ ለመደዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማታለል ቢሞክር እንኳን መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ መሆን ወይም መምሰል እንዳለበት በሚገባ ያዉቃል፤ ይህ ደግሞ ለመለስ ዜናዊ የሚዋጥ ሀቅ አይደለም። ለዚህ ነዉ ዛሬ አገር ፍቅር፤ብሔራዊ ጥቅም፤አባይ፤ ግብፅና አማፅያን በሚሉ አዳዲስ ቃላት የቆሸሸ ፊቱን ሸፍኖ ያላመሻሸበት ቤት አሳድሩኝ እያለ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚጨቀጭቀዉ።
ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጋዜጣዉ፤ሬድዮኑ፤ቴሌቭዥኑ እንዲሁም በየህንፃዉ ላይና በየመንገዱ ዳር ተሰቅለዉ የሚነበቡት ጽሁፎች ሁሉም የሚያስተላልፉት መልዕክት አንድ ነዉ – እሱም መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚቆረቆር አገር ወዳድ ሰዉ መሆኑን ነዉ። መለስ ዜናዊ በእርግጥ አገሩን የሚወድ ሰዉ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ማስታወቂያ ለምን አስፈለገዉ? የኢትዮጵያ ህዝብስ ጥዋትና ማታ ጥላቻ ብቻ እየተጋተ በተግባር አይቶት የማያዉቀዉን የመለስ ዜናዊን አገር ወዳድነት እንዲቀበል የሚገደደዉ ለምንድነዉ?
መለስ ዜናዊ ጠባብ ብሔረተኛ እንጂ ኢትዮጵያን የሚወድ ሰዉ አይደለም፤ ስራዉና ባህሪዩም በግልፅ የሚያሳዩት ይሀንኑ ነዉ። አገራቸዉን የሚወዱ ሰዎች ለአገራቸዉና ለህዝባቸዉ ያለቸዉ ፍቅር ከምንም ነገር ይበልጥባቻዋል፤ እንደ ወያኔ መሪዎች ብሔረተኛ የሆኑ ሰዎች ግን የኛ ነዉ ብለዉ ከሚጠሩት ህዝብ ዉጭ ለሌላዉ ህዝብ ጥላቻ እንጂ ፍቅር የላቸዉም። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍቅር፤መተሳሰብ፤ሰላም፤የዜጎች እኩልነትና የአገር አንድነት የዉኃ ሽታ የሆኑት ኢትዮጵያ የምትመራዉ በከፋፋዮችና በጠባብ ብሔረተኞች ስለሆነ ነዉ። በባድመዉ ጦርነት ላይ ከሌላዉ የኢትዮጵያ ክፍል የተመለመለዉ ወጣት ፈንጂ ፈታሽና ጥይት አብራጅ ሆኖ በመቶ ሺዎች ሲረግፍ መለስ ዜናዊ ወርቃማዉ ብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ የመጣዉ ወታደር ግን ከኋላ ቆሞ የገዛ ወገኖቹን ማስጨፍጨፉ የሚያሳየን ጦር ሜዳ ላይ የተከሰተ ስልታዊ ስህተትን ሳይሆን እነመለስ ዜናዊ ለሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸዉን ስር የሰደደ ጥላቻ ነዉ። ባለፉት ሃያ አመታት በኤኮኖሚ ኃብት ክፍፍልና በፖለቲካ ስልጣን ዙሪያ ያየነዉ እዉነታም ከባድመዉ ወታደራዊ እዉነታ የተለየ አይደለም።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልፅ መሆን ያለበት ይመስለናል፤ በአንድ በኩል ኢትዮጵያን ገፍቶ ገፍቶ ገደል አፋፍ ያደረሳት መለስ ዜናዊ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እቺ የብዙዎች እናት የሆነች አገር ገደሉ ዉስጥ እንዳትወድቅ የሚታገሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን አሉ። ስለዚህ ዛሬ ይህ ትዉልድ መመለስ ያለበት አንገብጋቢ ጥያቄ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ይወዳል ወይስ አይወድም የሚለዉን ጥያቄ አይደለም። የዘመናችን አቢይ ጥያቄ እቺን የምንወዳትን እናት አገር ከዘረኞችና ከቀማኞች የምናድናት መቼ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ ነዉ። ወደድንም ጠላን ወይ እኛ ልጆቿ አለዚያም ዛሬ ከአመታት በኋላ በአገር ፍቅር ተለከፍኩ የሚለን መለስ ዜናዊ ከሁለት አንዳችን የግድ ኢትዮጵያን መወደድ አለብን – አለዚያማ ሁላችንም ስለማንወደዉ አገር በጋራ ማዉራትም የለብንም። መለስ ዜናዊ ምን ያክል ኢትዮጵያን እንደሚወድ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ በአዲስ አበባ መንገዶች ከዚያም በፊት በደኖ፤አርባጉጉ፤ ጋምቤላ፤ኦጋዴን፤አዋሳና አምቦ ወስጥ በህዝብ ልጆች ላይ በወሰደዉ አረመኔያዊ እርምጃ አሳይቷል። እኛስ የኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደምንወድ እንዴትና መቼ ነዉ የምናሳየዉ?
ኢትዮጵያን ለዘመናት ቀስፎ የያዛት ችግር መንስኤዉ ሙሉ ለሙሉ መለስ ዜናዊ ነዉ ማለት ያስቸግር ይሆናል፤ ሆኖም ዛሬ ለኢትዮጵያ ቁስሏም መድሐኒቷም መለስ ዜናዊ ነዉ። ቁስል እንደሆነ የመቆየት ወይም መድሐኒት የመሆን ምርጫም የራሱ የመለስ ዜናዊ ነዉ። በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ታጋሽ ህዝብ ነዉና መለስ ዜናዊ ይህንን ለሱ ለራሱም ሆነ ለአገራችን ለኢትዮጵያ የሚበጃትን ምርጫ እንዲመርጥ ሃያ አመት ሙሉ ታግሶታል። ትዕግስት የጠንካራና የአስተዋይ ህብረተሰብ መለኪያ ቢሆንም – እንኳን በአገር ጉዳይ በትናንሹ የቤት ዉስጥ ጉዳያም ቢሆን ወሰኑን ገፍቶ ያለፈ ትዕግስት ያስደፍራል እንጂ አያስከብርም።አራት አመት ሙሉ በትዕግስት ሲለማማዱ የቆዩ የኦሎምፒክ የመቶ ሜትር ሯጮች ተነስ የሚላቸዉ የሽጉጥ ድምጽ አስኪሰማ ድረስ በትዕግስት ካልጠበቁ ከውድድሩ ዉጭ ይሆናሉ፤ አንዴ የሽጉጡን ድምፅ ከሰሙ በኋላ ግን ትዕግስቱ ያበቃና ጥረታቸዉ ሁሉ ባለጋራን ለማሸነፍ መክነፍ ነዉ። እኛም የኢትዮጵያ ልጆች መለስ ዜናዊን ሃያ አመት ሙሉ በትዕግሰት ጠብቀነዋል ከአሁን በኋላ ግን ሩጫችንና ትግላችን የዘረኛዉን የመለስ ዜናዊን ስርአት ለማስወገድ መሆን አለበት። ትዕግስት ሞልቶ ሲፈስ ምሬትን ይወልዳልና ከዛሬ በኋላ ለመለስ ዜናዊ ማሳየት ያለብን ትዕግስታችንን ሳይሆን ምሬታችንንና ቁጣችንን መሆን አለበት።የአገርንና የህዝብን ተስፋ ለጥቂት ዘረኞችና ከሃዲዎች ትቶ ምን አገባኝ ብሎ ከመቀመጥ የበለጠ ከሃዲነት የለም። ጠላቶቻችን እኛን ለመግዛትና አገራችንን እንዳሻቸዉ ለማድረግ የተጓዙትን ጉዞ እኛ ለነፃነታችንና ለአገራችን ክብር ስንል ለመጓዝ ፈቃደኞች ካልሆንን ኢትዮጵያዉያን ተብለን ልንጠራ አይገባም። የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያለዉ እጃችን ላይ ነዉ። ኢትዮጵያ ከሃያና ከሰላሳ አመት በኋላ ምን ትመስላለች የሚለዉን ጥያቄ በትክክል ለመመለስ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በአዲስ መልክ ለመገንባት የሚያሰችለንን የፖለቲካ ሥልጣን ከጥቂት ዘረኞችና ዘራፊዎች መዳፍ ፈልቀቀን አዉጥተን ለትክክለኛ ባለቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስረከብ አለብን። ኢትዮጵያዊነት ኩራት ነዉ፤ኢትዮጵያዊነት ሽንፈትን አለመቀበል ነዉ ኢትዮጵያዊነት ለአገርና ለወገን ክብር መቆም ነዉ ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬ ምርጫዉ አንድ ብቻ ነዉ – እሱም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳዉን ወያኔ የሚባል የዘረኞች ስብስብ ከአገራችን የፖለቲካ መድረክ ጠራርጎ ማዉጣት ነዉ።