የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር 267 የወያኔ ወታደሮችን ገድያለሁ ማለቱ ተዘገበ

ለረዥም አመታት የወያኔን አገዛዝ ሲዋጋ የቆየው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ባለፉት በርካታ ሳምንታት በአገዛዝ ጦር ላይ በከፈተው ጥቃት 267 ወታደሮችን መግደሉን እና 157 ማቁሰሉን እንደገለጸ ሬውተርስ የዜና አገልግሎት ድርጅት ዘግቧል።

የአገዛዙ ቃል አቀባይ ሽመልስ ከማል ጥቃቱ መፈጸሙን እንደ ወትሮው ክዷል።

ኦብነግ ሶማሊ ክልል ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የሚፈጽም ሲሆን፤ ቡድኑን ማጥፋት ያቃተው የወያኔ አገዛዝ ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው ተጉዘው የሚደርስበትን ጥቃት እንዳይመዘግቡ ከከለከለ አመታት ማስቆጠሩ ይታወቃል።

አካባቢው የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ፍለጋ ሲንቀሳቀስ የነበረው የማሌዥያ ኩባንያ ፔትሮናስ ይዞታውን ለሌላ ኩባንያ ሸጦ መውጣቱ ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት አገዛዙ በሽያጩ እንዲስማማለት እየጠበቀ ነው ሲል ሬውተርስ በዘገባው አመልክቷል። ፔትሮናስ የማእድን ፍለጋ ፕሮጀችክቱን ትቶ ለመውጣት የተገደደው ወያኔ በአካባቢው ጸጥታን ማስፈን ስለተሳነው ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ኦብነግ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ፤ የፔትሮናስን ይዞታ የገዛው ኩባንያ ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት አለው ማለቱ ይታወሳል።