የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ባለፈው አመት የምርጫ ተውኔት ላይ ባወጣው ሪፖርት የወያኔን አገዛዝ ክፉኛ አወገዘ

የህብረቱ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን የግንቦት 15፣ 2002ቱን የምርጫ ተውኔት ሪፖርት ከአምስት ወራት በኋላ በብራሰልስ ከተማ ይፋ ማድረጉን የዝግጅት ክፍላችን ባልደረባ ከስፍራው በላከው ዘገባ አሳውቋል።

ቡድኑ በዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ላይ ጠንካራ ሂሶችን የሚሰነዝረውን ሪፖርት በአዲስ አበባ ለማቅረብ ፈልጎ የመግቢያ ፈቃድ እንደተከለከለ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ ይህም በአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢነት የረዥም አመታት ልምድ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በኢትዮጵያ መሆኑን ሪፖርተራችን የቡድኑን መሪ ጠቅሶ ዘግቧል።

የግንቦት 15ቱን ምርጫ ተብዬ በማስመልከት የወጣው ሪፖርት፤ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ያለውን የሚያስረግጥ ሲሆን፤ ምርጫው አለማቀፍ መስፈርቶችን እንደማያሟላ፤ በተካሄደበት ወቅትም የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብና የውድድር ሜዳው ለገዢው ቡድን ያደላ እንደነበር መስክሯል። በተጨማሪም፥ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ገዢው ቡድን የመንግስት ንብረት ለምርጫ ቅስቀሳ ሲጠቀም እንደነበር፤ የግል መገናኛ ብዙሃን እና የሲቪኩ ማህበረሰብ ከደረሰባቸው አፈና የተነሳ መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ገልጿል።

የቆጠራ ሂደቱም ግልጽነት የጎደለው እንደነበር አስረድቷል። የታዛቢዎቹ ቡድን ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣው አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች “ሂውማን ራይትስ ዋች”፤ “እውነታዎቹ ለራሳቸው ይመሰክራሉ፦ አገዛዙ በግንቦት ወር 99.6 በመቶ የሚሆነውን መቀመጫ አሸንፌያለሁ ማለቱና፤ ሌላው ቀርቶ የታዛቢ ቡድኑ ሪፖርቱን አዲስ አበባ እንዲያቀርብ መፍቀድ አለመፈለጉ፣ ስር የሰደደውን ተቃውሞ እና ሂስ ያለመቀበል ባህሪውን ያጋልጣል” ብሏል።

“ሂውማን ራይትስ ዋች” ጨምሮም፥ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት፣ የአገዛዙ ካድሬዎች እና ሚሊሻዎች ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ ህዝቡ ገዢውን ቡድን እንዲመርጥ፤ ካልመረጠም እንደሚቀጣ እና፤ ይህም ቅጣት መኖሪያን ወይም ስራን መነጠቅን እንደሚያካትት እንደተነገረው ገልጿል።