አንድ የፌዴራል ፖሊስ ባለስልጣን መታሰሩ ተዘገበ
የፌዴራል ፖሊስ አባል እና የቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሰርቬላንስ ክፍል ሃላፊ የሆነ ግለሰብ በሙስና ምክንያት መታሰሩን አፍሪክ ኒውስ የተባለው የዜና ድረ-ገጽ ዘግቧል።
ሳጅን ማሞ ሻሎ የተባለው ግለሰብ አንዲትን ሴት በሽብርተኝነት ታስራ እንደምትከሰስ ነግሮ እራሷን ለማዳን ስትል ጉቦ እንድትሰጠው በማስፈራራቱ ምክንያት መታሰሩን በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የጸረ-ሙስና ኮሚሽን እንደገለጸ ዘገባው አስረድቷል።
ሴቲቱ አስር ሺህ ብር እንድትሰጠው ያስማማት ሳጅን ማሞ፣ የተወሰነውን ክፍያ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙንም ኮሚሽኑ ተናግሯል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከወያኔ ባለስልጣናት ትእዛዝ ውጪ እንደማይንቀሳቀስ ይታወቃል። የዝግጅት ክፍላችን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሳጅን ማሞ ሻሎን ጉዳይ ከገለልተኛ አካል ለማጣራት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የወያኔ አገዛዝ ባለፈው አመት ያጸደቀው የጸረ-ሽብርተኝነት ተብዬ ህግ ዜጎችን ለማሰር ማንኛውም የፖሊስ አባል በሽብርተኝነት ቢወቅሳቸው በቂ ነው ይላል።