አዜብ መስፍን የሰበታ ከተማ ሰራተኞችን አሰረች
የዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ባለቤት እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ወይዘሮ ሙስና” የሚል ቅጽል ስም የወጣላት አዜብ መስፍን ወደ ሰበታ ከተማ ሄዳ በርካታ የከተማ አስተዳደሩን ሰራተኞች በግል እንዳሳሰረች ለግንቦት 7 የደረሰ መረጃ አመልክቷል።
በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን የምትገኘው የሰበታ ከተማ መስተዳደር፥ ከአየር በአየር የመሬት ንግድ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ደረጃ በሙስና ውስጥ የተዘፈቀ እንደሆነ እና አዜብ እራሷ በሺዎች የሚቆጠር ካሬ ሜትር መሬት በአካባቢው እንደተሰጣት ምንጮቻችን ጠቁመዋል። የከተማዋ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች ጉቦ እየተቀበሉ መሬት በማደል ከብረው አንዳንዶቹ በአስርተ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር እንዳካበቱ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ለግንቦት 7 ምንጮቻችን ተናግረዋል።
በተለይ በቅርብ ጊዜ ከአሜሪካን አገር የሄደ ግለሰብ፣ ጉቦ ሰጥቶ የግንባታ ስራ ለማከናወን በሚል አምስት መቶ ባለ አምስት መቶ ካሬ ሜትር መሬት መመራቱን፤ ነገር ግን ምንም ግንባታ ሳያከናውን መሬቱን በሙሉ ሸጦ ከአገር መውጣቱን ምንጮቻችን ገልጸዋል። በከተማዋ የነገሰው ሙስና አዜብን ጨምሮ በአገዛዙ ባለስልጣናት የታወቀ እንደነበረና፤ ከመሬት መስተዳደሩ መሃንዲሶች ውስጥ በተለይ አንዷ የአባ ዱላ ገመዳ የቀኝ እጅ እና የሙስና አቀናባሪ እንደነበረች ለማወቅ ተችሏል።
ይሁን እንጂ፥ የአሜሪካን አገሩ ግለሰብ ጉዳይ በባለስልጣናቱ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ አንዱ ቱባ ባለስልጣን “ተላጥን” ሲል ተሰምቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለም በርካቶቹ የከተማዋ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች የስራ መልቀቂታ ያስገቡ ሲሆን፤ ሁለቱ አገር ጥለው ለመውጣት ሲሞክሩ ቦሌ አየር ማረፊያ ላይ ተይዘዋል። ከቁጥጥሯ ውጪ የሆነ ሰው ከሙስናው መጠቀሙ ያናደዳት አዜብ መስፍንም፤ በግል ወደ ሰበታ ከተማ ሄዳ የተቀሩትን አስለቅማ ማሳሰሯ ታውቋል።
አዜብ የፓርላማ አባል እና የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ከመሆኗ በስተቀር በፖሊስ ሃይሉ ወይም በጸረ-ሙስና ኮሚሽን ውስጥ ምንም የታወቀ ስራ የላትም። በጉዳዩ ላይ ያናገርናቸው አስተያየት ሰጪ፥ ሴትየዋ አገሪቷን እንዳሻት ማሾሩን እንዳጠናከረችበት ያሳያል ብለዋል።
ጨምረውም፥ “አገዛዙ ሙስና እንዲካሄድ የሚፈቅደው የራሱን ባለስልጣናት ለመጥቀም እና ሰዎችን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ሆኖ ሳለ፤ እነዛ የሰበታ ከተማ ሰራተኞች ግን ገንዘባቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ከቁጥጥሩ ለመውጣት መሞከራቸው ነው ስህተታቸው” ብለዋል። “እነ አዜብ የይለፍ ፈቃድ ላልሰጡት የዳያስፖራ ሰው ያን ያህል መሬት አንስተው መስጠታቸው ሳያንስ፤ ከአገር ለመውጣት መሞከራቸው ለሌሎች የአገዛዙ ካድሬዎች መጥፎ ምሳሌ ስለሆነ ከአሁኑ መቀጣጫ መደረግ ነበረባቸው” ሲሉም አብራርተዋል።
የአየር በአየር የመሬት ንግድ ከቁጥጥሩ መውጣቱን የተገነዘበው ወያኔ፤ አዲስ የመሬት አዋጅ እንዳወጣም ለማወቅ ተችሏል።