የትግራዩን ገዢ ጉጅሌ ከሥልጣን ማባረር ሃገራችንን ከድንቁርና ነፃ የማውጣት ትግል አካል ነው!!!

የሰለጠነ የሰው ኃይል ለልማት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቀዳሚው መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። የልማት ፍሬዓማነት መለኪያ ከሆኑ አመልካቾችም አንዱ የሰለጠነ የሰው ኃይል የመፍጠር አቅም መገንባቱ ነው።

ሃገር እንድትበለጽግ ከተመጽዋችነትና የበታችነት መንፈስ መላቀቅና በራስ የመተማመን ስሜት መገንባት ይገባል። በራስ የመተማመን ስሜት የሚገነባው ደግሞ የራስ የሆነን ነገር በማክበር እና የራስን አቅም በመገንባት ነው። ይህም ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል መገንባትን፤ የተገነባውን መንከባከብን እና በአግባቡ መጠቀምን ይጠይቃል።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ኢትዮጵያዊውን ባለሙያ አያምንም። ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ወይም ምሁር በጉጅሌው ካድሬዎች የሚንጓጠጥ፣ የሚጉላላ፣ የሚሰደብና የሚረገጥ እንጂ በአገሩ ጉዳይ የሚናገር፤ ስለ አገሩ የሚቆረቆር መሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊ ባለሙያና ምሁር የካድሬ መጫወቻ ነው። የትግራዩ ጉጅሌ በጉልበት ሥልጣን ከያዘበት እለት ጀምሮ በእውቀትና በአዋቂዎች ላይ ዘምቷል።

እውቀትንና አዋቂዎችን ከማጥፋት ጎን ለጎን ደግሞ የራሱን ትንሽነት መደበቂያ መንገድ ፈጥሯል። “እኔም የተማርኩና የተመራመርኩ ነኝ” በማለት የዝቅተኝነት መንፈሱን ለማስታመም ጉጅሌው ራሱን በግዢ በተገኙ የትምህርት ማስረጃዎች አንበሻብሿል። የሃገሪቱ የትምህርት ሥርዓትም እሱ ራሱ የያዛቸውን ዓይነት ባዶ ወረቀቶችን ማደያ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት አገራችን ውስጥ ሙያም ባለሙያም ተዋርዷል። በዘመነ ወያኔ “የተማረ ነው” መባል የስድብ ያህል አሳፋሪ ሆኗል።

በእውቀትና በአዋቂዎች ላይ የተደረገው ዘመቻ ውጤት በየእለቱ እያየነው ነው:-

  • ፍርድ ቤት ስንሄድ በስልክ እየተነገረው የሚፈርድ ዳኛ ችሎት ላይ ተኮፍሶ እናገኛለን፤
  • የፍሳሽ ማውረጃ የሌላቸው ፎቆችን እየገነባ ያለ መሃንዲስ በጥበቡ ብዛት ይራቀቅብናል፤
  • መርፌ በወጉ የማይወጉ ሃኪሞች በበሽተኞች ላይ ይዘባበናሉ፤
  • ለተማሪዎቻቸው የሰጡትን ፈተና እራሳቸው ቢፈተኑ የማያልፉ መምህራን “ከኔ ባላይ ላሳር” ሲሉ ይገኛሉ።

በእንዲህ ዓይነት “የተማረ” ሰው ኃይል እድገት ሊመጣ ቀርቶ አሉበት መቆየትም አዳጋች ነገር ነው።

በአንፃሩ ቀድሞ የነበረው የትምህርት ሥርዓት በርካታ ድክመቶች የነበሩበት ቢሆንም በሙያቸው የተከበሩ ጥቂት ምሁራንን አፍርቷል። የመጀመሪያው አፍሪቃዊ አይሮፕላን አብራሪ፣ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ የስልክ ቴክኖሎጂ ባለሙያ፣ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካዊያን የስነ-መንግሥት ምሁራን ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን በቴክኒክ ኮሌጅ የሚሰጡ ትምህርቶች በሰለጠኑ አገሮች ከሚገኙ ተቋማት ጋር መሳ ለመሳ የሆነ ተቀባይነት ነበራቸው። ምሩቃኑም ሙያ ብቻ ሳይሆን የአገር ፍቅር ስሜት የተላበሱ ነበሩ። እነማንዴላን ጨምሮ ኢትዮጵያ ለብዙ አፍሪካዊያን አርዓያ ነበረች። አሁንም ቢሆን የዚያ ወቅት አሻራ ያረፈባቸው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች አሉ። እነዚህ ባለሙያዎች የሚገኙት ግን አሜሪካና አውሮፓ እና ሌሎች አገሮች ውስጥ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም። ሙያቸውን ጠንቅቀው ያወቁ፤ በራሳቸው የሚተማመኑ ባለሙያዎች ሁሉ ተገፍተው አገር ለቀው እንዲሰደዱ በመደረጋቸው ኢትዮጵያ ልትመካባቸው የሚገቡ ባለሙያዎች የሚገኙት በውጭ አገራት ውስጥ ነው።

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በየክልሉ ለህንፃዎች የዩኒቨርስቲነት ስያሜ መስጠቱን እናውቃለን። ወደ እነዚህ ህንፃዎች የሚመላለሰውም ወጣት ቁጥር በብዙ መጨመሩ እውነት ነው። ሆኖም ባለሙያ ሲያፈሩ ግን አልታዩም፤ ለዚህ ተግባር የተፈጠሩም አይደሉም።

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ያለበትን የእውቀት ማነስ የህዝብ ንብረት ለመሸጥ በምክንያትነት ሲያቀርብ መስማት ደግሞ ሌላው አስገራሚ ነገር ነው። ለምሳሌ:-

  • መሬትን በገፍ ለመሸጥ የሚያቀርበው ምክያት “ግብርናውን የማዘመን አቅምም ችሎታም የለንም” የሚለው እንደሆነ ልብ ይሏል። “ኢትዮጵያዊያን የግብርና ባለሙያዎች የት ገቡ?” ብሎ መጠየቅ አይቻልም። እንዲያም ሆኖ ግን “የግብርና ባለሙያዎችን በገፍ እያሰለጠንኩ ነው” እያለ ይቦተልካል።
  • “የማዕድን ሃብታችን ለማልማት የሚጠይቀው እውቀትና አቅም የለንም” የሚለው ሰበብም ቱጃሩን እየጠቀመ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ዛሬ የአገራችን የወርቅ ማዕድን በቱጃሩ ግለሰብ እጅ ውስጥ ገብቷል።
  • አሁን ደግሞ “የማኔጅመንት ባለሙያ የለንም” በሚል ሰበብ ኮርፓሬሽኖችን መሸጥ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ማኔጅመንት ለፈረንሳይ ኩባንያ መሰጠቱ በመሬት የተጀመረው ሽያጭ ወደ ኩባንያዎች የመምጣቱ መርዶ ነጋሪ ነው። የሚቀጥሉት ተረኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የኤለክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንደሚሆኑ መጠበቅ ይቻላል።

ግንቦት7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ በድንቁርናው በመኮፈስ ላይ ያለው፤ ፀረ-እውቀት እና ፀረ-አዋቂ የሆነው የትግራዩን አምባገነን ገዢ ካሰፈነብን የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እስካልወጣን ድረስ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሊኖር ይችላል ብሎ አያምንም። ስለሆነም የትግራዩን አምባገነን ገዢ ጉጅሌ በጋራ አስወግደን ሃገራችን ከገባችበት የድንቁርና አዘቅት እናውጣ እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!