የአለም ባንክ ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ መጠን ብሔራዊ ባንክ ከሚለው በሶስት እጥፍ ይበልጣል አለ
የአለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት ኢትዮጵያ በየአመቱ ውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የምታገኘው ገንዘብ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ነው ማለቱን አፍሪክ-ኒውስ የተባለው የዜና አውታር ዘግቧል።
ይህ ቁጥር በወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ያለው ብሔራዊ ባንክ በየአመቱ ከሚያስቀምጠው በእጥፍ ድርብ የሚበልጥ ነው፤ ብሔራዊ ባንክ በየአመቱ ከስደተኛው ማህበረሰብ የሚገኘውን ገንዘብ ከቢሊዮን ዶላር በታች እንደሚያኖረው ለማወቅ ተችሏል። የአለም ባንክ ጥናት፥ 14 በመቶ የሚሆኑና ለአቅመ አዳም የደረሱ ኢትዮጵያውያን በአመት ቢያንስ 600 ዶላር ከውጭ አገር እንደሚላክላቸውም ገልጿል።
ከደካማ የመረጃ አሰባሰብ መዋቅር በተጨማሪ፣ በአገዛዙ ቁጥጥር ስር ያለው ብሔራዊ ባንክ ቁጥሩን አሳንሶ የሚናገርበት ፖለቲካዊ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላል ያሉን የፖለቲካ ተንታኝ፥ እውነተኛውን ቁጥር መናገሩ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሃይላቸውን እንዲረዱ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ስደተኞቹ በአብዛኛው ወያኔን እንደሚቃወሙ እና ለአገዛዙ የእግር እሳት ሆነው እንደቆዩ ይታወቃል።
የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት፣ ይህ ትልቅ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ በእጁ ያለውን ሃይል ከተረዳ ለወያኔ አደገኛ ሊሆንበት ይችላል። ጉዳዩን ከህዝብ ቁጥር ጋርም አወዳድረውታል። ባለፈው አመት በወጣው የህዝብ ቆጠራ ውጤት፣ አገዛዙ የአማራን እና የአዲስ አበባን ህዝብ ቁጥር አሳንሶ ማቅረቡ ይታወሳል።