በመቶዎች የሚቆጠሩ የአራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው ታወቀ
ለሸራተን ሆቴል መስፋፊያ ይሆን ዘንድ ከመኖሪያዎቻቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ዜጎች በሆቴሉ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን – ኢሳት – የተገኘው ዘገባ እንደሚጠቁመው፣ እሁድ ጥቅምት 16 ቀን ከ500 በላይ የሚሆኑ የአራት ኪሎ ነዋሪዎች በሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ፍትህ ለመጠየቅ ተሰባስበው ነበር። ነዋሪዎቹ በቂ መጠለያ ሳይዘጋጅላቸው እየተፈናቀሉ እንደሆነና የሚከፈላቸው ካሳ እንኳን ሌላ ቤት ሊያስገነባ አንድ መኝታ ቤት ያለው ኮንዶሚኒየም ለመግዛት እንኳ እንደማይበቃ በመናገር አማረዋል።
ስሞታቸውን ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ለማቅረብ የሞከሩት ተፈናቃዮች፤ “እናንተ የልማት አደናቃፊዎች ናችሁ” የሚል መልስ እንደተሰጣቸውም ዘገባዎቹ ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ ምንም እንኳ የዘረኛውን አምባገነን ፎቶግራፍ እና ከፍትህ በስተቀር ምንም እንደማይፈልጉ የሚጠቁሙ መፈክሮች ተሸክመው ቢወጡም፤ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሃይሎች በስፍራው ተገኝተው ሰልፉን መበተናቸው ታውቋል።
ዜጎቹ እንደገና በመሰባሰብ ሰልፋቸውን ለመቀጠል ሲሞክሩም፤ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አስራ አንድ ወንዶችን እና ሁለት ሴቶችን የረብሻው መሪዎች ናቸው በሚል ማሰሩን የአዲስ ነገር ኦንላይን ዘገባ አሳይቷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ ከእስረኞቹ አስሩ መፈታታቸውን እና ሶስቱ ግን “ህገ-ወጥ ስብሰባ በመቀስቀስ እና የመንግስት ልማታዊ ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ የታለሙ ህገ-ወጥ ሰልፎችን በመምራት” በሚል እንደሚከሰሱ ይኸው ዘገባ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ከተሞች፣ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በልማት ስም በሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች በቂ ካሳ ሳይሰጣቸው እየተፈናቀሉ እንዳሉ ይታወቃል።