በወያኔ ቁጥጥር ስር የምትገኘው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል ተብለው ከሚታመኑ አገሮች ተርታ ትመደባለች ተባለ

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው እና በአለም አገራት ያለውን ሙስና የሚለካ ሪፖርት የሚያወጣው ድርጅት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ሙስና አለባቸው ተብለው ከሚገመቱ አገራት ተርታ አስቀምጧታል።

ድርጅቱ በአመታዊ ሪፖርቶቹ፥ ህዝቦች በየአገራቸው በመንግስት ባለስልጣናት ዘንድ ሙስና አለ ብለው የሚያምኑበትን ደረጃ ይመዝናል። በዚህም አኳኋን ከአንድ እስከ አስር ባለው ደረጃ፤ አንድ ቁጥር ከፍተኛ ሙስና ሆኖ አስር ቁጥር ደግሞ ዝቅተኛ ወይም ምንም ሙስና ሲሆን፤ ኢትዮጵያ 2.7 በማግኘት ከአለም 116ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ድርጅቱ ለሪፖርቶቹ የሚጠቀማቸውን መረጃዎች በአብዛኛው የሚያገኘው የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ካካሄዷቸው ጥናቶች እና አሰሳዎች እንደሆነ ይጠቅሳል። በአሰሳዎቹ የሚዳሰሱት ጥያቄዎችም ለመንግስት ባለስልጣናት ጉቦ መስጠት፤ የመንግስት ኮንትራክት ከማግኘት ጋር ተያይዞ የሚሰጥ ጉርሻ፤ የህዝብ ንብረት መስረቅ፤ እና የጸረ-ሙስና እንቅስቃሴዎችን ጥንካሬ ደረጃ መመዘን በሚሉ ሃሳቦች ዙሪያ እንደሚያጠነጥኑ የተቋሙ ድረ-ገጽ ያስረዳል።