የወያኔ አገዛዝ በአራት የትጥቅ ቡድኖች ጥምረት መመስረት ላይ ያወጣው መግለጫ የባለስልጣናቱን መረበሽ አንጸባርቋል ተባለ
የዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ በተመሰረተው የትጥቅ ቡድኖች ጥምረት ላይ ያወጣው መግለጫ በርካቶችን ግራ አጋብቶ የሰነበተ ሲሆን፤ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በአገዛዙ ዘንድ ያለ ያለመረጋጋት ነጸብራቅ ነው ብለውታል።
“ጥምረት የኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ለውጥ” የተባለ እና አራት የትጥቅ ቡድኖችን ያካተተ ህብረት መፈጠሩን የምስረታውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባውን ያስተላለፈው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት – ኢሳት – የጥምረቱ መስራቾች፦ “የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህና እኩልነት ግንባር” መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ዘግይቶ መግለጫ ያወጣው የወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአንድ ጎን ቡድኖቹን የወደቁ ብሎ ሲያጠቃ፤ ይህንኑ ሊናገር ግን በቁጣ የተሞላ ሶስት ገጽ ጽሁፍ ማውጣት ለምን እንዳስፈለገው ግልጽ አላደረገም። እርስ በርሱ የሚጣረሰው ጽሁፍ ጨምሮም፤ እነዚህ የሞቱ እንደሆኑ የተነገረን ቡድኖች በአገዛዙ ላይ የደህንነት ችግር እንደሚፈጥሩ ይገልጻል።
መግለጫው ለጥምረቱ መመስረት የኤርትራን መንግስት የሚወነጅል ሲሆን፤ “ይህ የህዝቦቻቸው በዘረኛው አገዛዝ መገፋት እና መታፈን በቅቷቸው ወያኔን ለመዋጋት የተነሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ቡድኖች መኖራቸውን ለመካድ አገዛዙ የሚያደርገው ሙከራ አካል ነው” ሲሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።
እኒሁ ግለሰብ ጨምረውም፥ የወያኔ አገዛዝ እውነት መግለጫው እንደሚለው ቡድኖቹ የሞቱ ናቸው ብሎ ቢያምን እንደዚህ ቁጣ በተሞላበት መልኩ፤ ታላቅ ቀውስ የተከሰተ ይመስል ረዥም መግለጫ ባላወጣ ነበር ብለዋል። መግለጫው፥ በአገዛዙ ላይ ያለው ስር የሰደደ አለመረጋጋት ስሜት ነጸብራቅ ነውም ሲሉ አብራርተዋል።