በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰቆቃ ድርጊቶች አሳስበውኛል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል ገለጸ
“ኮሚቴ አጌነስት ቶርቸር” የተባለው እና የተባበሩት መንግስታት ጸረ-ሰቆቃ ስምምነቶች በስራ ላይ መዋላቸውን እንዲከታተል የተመሰረተው አካል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚፈጸሙ የሰቆቃ ድርጊቶች ስጋቱን ገልጿል።
እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1987 በስራ ላይ የዋለው ይህ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ስምምነት፤ አገራት በድንበራቸው ውስጥ የሰቆቃ ድርጊት እንዳይፈጸም ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እና ከሌላ አገር ሰቆቃን ሸሽቶ የመጣን ሰው ወደመጣበት አገር እንዳይመልሱ ያዛል። ኢትዮጵያውም ከሰባት አመታት በኋላ የስምምነቱ አካል ሆና ነበር።
በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ሪፖርት ማቅረብ የነበረበት ሲሆን፤ አስራ አራት አመታት ዘግይቶ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ መቅረቡን ኮሚቴው ጠቅሷል። ከኢትዮጵያው አገዛዝ ጎን ለጎን የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ ኮሚቴውም የቀረበለትን መረጃ መርምሮ ድምዳሜውን አውጥቷል።
በዚህ አኳኋንም፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖሊስ፣ በእስር ቤት ሰራተኞች እና በደህንነት አካላት የሚፈጸሙ በርካታ የሰቆቃ ድርጊቶች እንዳሉ እና፤ በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ በተማሪዎች እና በሽብርተኝነት እና የትጥቅ ቡድኖችን በመደገፍ በሚጠረጠሩ ላይ እንደሚደርሱ መረጃዎች እንደደረሱት ጠቅሷል። በፖሊስ ጣቢያዎች እና እስር ቤቶችም ውስጥ ዜጎችን አስገድዶ ለማናዘዝ ሰቆቃን መጠቀም የተለመደ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች እንዳሉ ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም፥ እነዚህን ወንጀሎች በሚፈጽሙት የአገዛዙ ቅጥረኞች ዘንድ ተጠያቂነት እንደሌለ እና ድርጊቱን በማናለብኝነት እንደሚያካሄዱ፤ እንዲሁም ለእስረኞች በቂ ጥበቃ እንደማይደረግ ዘርዝሯል። ገለልተኛ አካላት እስር ቤቶችን ለመጎብኘት አለመቻላቸውንም መስክሯል። ከሰቆቃ ሌላም፥ በአገሪቱ ዙሪያ ህገ-ወጥ ግድያዎች፣ አፈናዎች፣ እና ህገ-ወጥ እስሮች መካሄዳቸው፤ እንዲሁም የአገዛዙ ጦር በሶማሌ ክልል ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈርን ወንጀል መፈጸሙ ክፉኛ እንዳሰጋው ገልጿል።