አሜሪካ በሙስና በተዘፈቁ ገዢዎች ገንዘብ ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር እያጠናከረች ነው

የዩናይትድ እስቴትስ መንግስት በሙስና የተዘፈቁ አገዛዞች እና ተወካዮቻቸው በሚያደርጉት የገንዘብ ዝውውር ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እያጠናከረ መሆኑን እና ባንኮች መስመር እንዲይዙ ትእዛዝ መተላለፉን “ዘ ዋል እስትሪት ጆርናል” የተባለው ታዋቂ የአሜሪካን አገር ጋዜጣ ዘግቧል።

ከዚህ አኳያ የተወሰዱ እርምጃዎችም በበርካታ ባንኮች ዘንድ ስጋትን እንደፈጠሩ እና አንዳንዶች ለበርካታ አገራት ኤምባሲዎች አገልግሎት መስጠት ማቆም እንደጀመሩ ዘገባው አመልክቷል። ባንኮቹ መንግስት የሚፈልጋቸውን የቁጥጥር መስፈርቶች በስራ ላይ ለማዋል የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አንድያውኑ ለዲፕሎማቲክ ተቋማቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ማቋረጡን መርጠዋል ተብሏል።

ከስድስት አመታት በፊት የሚሺጋን ግዛት ተወካይ ሴኔተር ካርል ለቪን “ሪግስ ናሺናል” የተባለ ባንክ ለቀድሞው የቺሊ አምባገነን ኦገስቶ ፒኖቼ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ደብቆ እንደነበር በማጋለጣቸው ባንኩ መውደቁን ዘገባው አስታውሷል።

አሜሪካ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2001 ከደረሰባት የሽብርተኞች ጥቃት በኋላ ጥብቅ የገንዘብ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን መቅረጿን የጠቆመው “ዘ ዋል ስትሬት ጆርናል”፤ በወቅቱ ከወጡት ህጎች አንዱ በሌሎች አገራት ከተካሄደ ሙስና የተገኘን ገንዘብ እያወቁ መቀበልን ወንጀል አድርጎታል ብሏል። የውጭ አገር ባለስልጣናት፣ ዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው በሚከፍቷቸው የባንክ ሂሳቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግም ያዛል። እነዚህ ህጎች ግን እስካሁን ድረስ በተገቢው መንገድ በስራ ላይ ያልዋሉ ሲሆን፤ የህግ አውጪዎች እና የገንዘብ ተቆጣጣሪዎች በአሁኑ ሰዓት ግፊታቸውን እንደጨመሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያው ዘረኛ አገዛዝ ባለስልጣናት የስልጣን መንበራቸው ሲፈርስ ወደ ውጭ አገራት ለመሸሽ ካላቸው እቅድ የተነሳ እስከ ቢሊዮን ዶላር እና ከዛም በላይ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ወደ ውጭ ባንኮች እንዳሸሹ ታማኝ ምንጮች ይናገራሉ።