ፔን ኢንተርናሽናል የአንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛን እስር በመቃወም መግለጫ አወጣ

የአስራ ሰባት አመቱ ወጣት እና የአልቁድስ ጋዜጣ ጊዜያዊ አዘጋጅ አክራም ኢዘዲንን እስር በመቃወም ፔን ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት መግለጫ አውጥቷል።

አክራም፥ “አል ቁድስ” የተባለው እና በአዲስ አበባ የሚታተመው የእስልምና ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ኢዘዲን ሙሃመድ ልጅ ነው። አቶ ኢዘዲን ባለፈው አመት መለስ ዜናዊ ለአንድ የእንግሊዝ አገር ጋዜጣ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ የተናገረውን በማውገዛቸው ታስረው የአንድ አመት ፍርድ ተቀብለው ነበር።

አባቱ ሲታሰሩ የጋዜጣውን የአዘጋጅነት ስራ የተረከበው አክራም፣ የአፋር ክልልን የእስልምና ምክር ቤት ስራ በማውገዙ በመስከረም ወር አሳይታ ተወስዶ ታስሯል። ወጣቱ አራት ጊዜ ፍርድ ቤት ቢቀርብም እስካሁን ክስ እንዳልቀረበበት ለማወቅ ተችሏል።

ፔን ኢንተርናሽናል የአክራም እስር ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን የሚጥስ በመሆኑ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቅ ጥሪ አቅርቧል። ክስ ሳይቀርብ አስሮ ማቆየት በአገሪቱ ህግ መሰረት ህገ-ወጥ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫ፤ ጋዜጣው ብሔራዊ በመሆኑም፣ ማንኛውም ክስ ሊቀርብበት የሚገባው በፌዴራል እንጂ በክልል ፍርድ ቤት አይደለም ብሏል።