የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አዲሱን ፓርላማ ህገ-ወጥ ብሎታል

ባለፈው ሳምንት ስራውን የጀመረው አዲሱ የመለስ ዜናዊ ፓርላማ “ህገ-ወጥ” ነው ሲሉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ታዴዎስ ቦጋለ መናገራቸውን ጅማ ታይምስ የተባለው የዜና ድረ-ገጽ ዘግቧል።

ዶ/ር ታዴዎስ አዲሱ ፓርላማ የቆመው በተሰረቀ ምርጫ ላይ እንደመሆኑ “ህገ-ወጥ ነው” ማለታቸውን ዘገባው አሳውቋል። ዶ/ር ታዴዎስ ሊቀመንበር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት በኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ይመራ የነበረው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፤ መድረክን ጨምሮ ከበርካታ የተቃዋሚ ሃይሎች የደረሰበትን ሂስ ወደጎን በተመው እና ከልደቱ አያሌው ፓርቲ ጋር በመሆን በስነ ምግባር ደንብ ተብዬው ላይ ከወያኔ ጋር ስምምነት መፈጸሙ ይታወሳል።

ከግንቦት 15 በኋላ ግን ፓርቲው የተካሄደውን የምርጫ ተውኔት ዘረፋ ብሎታል። እንደ መድረክ ካሉት ጋር በመሆን ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቦም ሳይሳካለት እንደቀረ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የቴዲ አፍሮ ጠበቃ እና ወያኔን በመወከል የፍቼን ህዝብ ድምጽ የዘረፈው ሚሊዮን አሰፋ አዲሱን ፓርላማ “ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁሉ የተሻለ” እንዳለው አዲስ ነገር ኦንላይን ጎግል ጋዜጣን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከጎግል ጋዜጣ ጋር አጭር ቃለ መጠይቅ ያደረገው ሚሊዮን አሰፋ፥ ተቃዋሚዎች ፓርላማው ውስጥ ቢኖሩ ህግ የማሳለፍ ስልጣን ስለማይኖራቸው፣ ዝም ብለው በፓርላማው ከመደመጥ ውጪ ምንም ጥቅም እንደማይኖራቸው እና፤ አሁን አለመኖራቸው ገዢው ቡድን እነሱን በማዳመጥ የሚያሳልፈውን ጊዜ ባቀዳቸው ነገሮች ላይ እንዲያውል እንደሚያስችለው፤ ስለዚህም ይሄ ከሁሉም ፓርላማዎች የተሻለ እንደሆነ ተናግሯል።