በኢትዮጵያ የተካሄደው መተካካት የዘረኛውን አምባገነን ስልጣን ከማጠናከር ውጪ አዲስ ነገር አያመጣም ተባለ
ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ አንዳንድ የቆዩ ባለስልጣናቱን ሽሮ አዳዲስ ካድሬዎቹን መሾሙ የራሱን ስልጣን ከማጠናከር ውጪ የሚያመጣው አዲስ ነገር የለም ሲሉ ምሁራን ተናግረዋል።
መድረክ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ አመራር አባል እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት ቃል ሲናገሩ፥ አዲሶቹ ሹመኞች በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ችሎታም ሆነ አስተሳሰብ ያላቸው አይደሉም። ዶ/ር መረራ “ያልበሰሉ” የሚሏቸው ካድሬዎች የተሾሙበት ምክንያት የመለስን ስልጣን ለማጠናከር ስለሚረዱ ነው።
ከሶስት ሳምንታት በፊት ለዚሁ የዜና አውታር ቃላቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኝ እና ምሁር አቶ መድሃኔ ታደሰ፥ መለስ ዜናዊ የትግል ጓዶቹን ከዙሪያው አስወግዶ የራሳቸው የድጋፍ መሰረት በሌላቸው አዳዲስ ሰዎች መተካቱ የሱን ተጽእኖ ያጠናክረዋል፤ የግል ሃሳቦቹም የአገሪቱን ፖለቲካ መቆጣጠራቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል። አቶ መድሃኔ ጨምረውም፥ በኢትዮጵያ የጋራ አመራር ከአመት አመት እየቀነሰ ሄዶ አሁን መለስ ዜናዊ የመንግስትም የገዢው ፓርቲም ማእከል ሆኗል ብለዋል።
ግንቦት 7 ንቅናቄ መለስ ዜናዊን ከሩሲያው ኮሚኒስት መሪ ስታሊን ጋር ባነፃጸረበት የመጋቢት 30፣ 2002 ርእሰ አንቀጹ እንዲህ ማለቱ ይታወሳል፡- “ስታሊን በመንበረ ሥልጣኑ ለመደላደል እንዲያመቸው የቀድሞ የትግል አጋሮቹን…አባሮ በትግሉ ውስጥ ያልነበሩትን…በመተካት እሱ ብቻ የትግሉ አባት ሆኖ መታየት የቻለ ሰው ነበር።…መለስም አብረው የታገሉትን የበረሃ ጓደኞቹን እነ ተወልደን፣ ሰለሞንን፣ አረጋሽን፣ ገብሩ፣ ፃድቃንና ስየን ከገፈተራቸው ቆይቷል። አሁን ደግሞ ስዩም፣ ፀጋዬ፣ አባዲ፣ አርከበ፣ ቴዎድሮስ፣ አዲሱና ተፈራ ተደግሶላቸዋል። መለስ እንደ ሬድዋን ሃሰን፣ ኃይለማርያም፣ መሃመድ ድሪር፣ ተሾመ ቶጋ፣ ሙክታር ከዲር፣ ድሪባ ኩማ እና ጁነዲን ሳዶ በመሳሰሉ እንደ ነቢይ በሚቆጥሩት ሰዎች እየታጠረ ነው።”