ለአዜብ መስፍን የቀራት የበርበሬ ንግድ ብቻ ነው
ከዝግጂት ክፍላችን
“ወደ ውጭ አገራት ስትሄድ እና እንግዶችን ስትቀበል ሚስትህን ከጎንህ የማታኖርበት ምክንያት ምንድን ነው?” ተብሎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥያቄ የቀረበለት መለስ ዜናዊ፤ “አይ እሷ ዝም ብላ ተራ የቤት ሚስት መሆን አትፈልግም፤ የፓርቲ አባል ከመሆኗ በተጨማሪ የራሷ ንግድ አላት፤ እናም በዛ ላይ መስራት ትፈልጋለች። እሷ የራሷን ንግድ ስትሰራ እኔ ደግሞ የመንግስት ስራዬን ስሰራ እንቆይና ኋላ ላይ ተገናኝተን የጋራ የቤተሰብ ስራችንን እንሰራለን፤” ማለቱን ሰማን።
ወሬው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተቀድቶ፣ በነጋድራስ ጋዜጣ ተጠቅሶ፤ በአዲስ ነገር ኦንላይን ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ፤ በኛ ደግሞ መልሶ ጭብጡ ወደ አማርኛ ዞሮ የቀረበ ነውና ሰውየው የተናገረውን ቃል በቃል አልያዝን ይሆናል፤ ጉዳዩ ውስብስብ ስላልሆነ ግን ከተናገረው ጭብጥ ሊርቅ እንደማይችል እርግጠኞች ነን።
እንግዲህ በገዢው ቡድን ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን እንዴት እንደሚሰሩ ለምናውቅ፣ መለስ ዜናዊ የተጠየቀውን ጥያቄ ከመጠየቁ በፊት እንዳየው እና ምናልባትም ጥያቄውን ራሱ እንዲጠየቅ የፈለገው እሱው እንደሆነ መገመት እንችላለን። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይህንን ጥያቄ እንዲጠይቀው ለምን እንደፈለገ ወይም እንደፈቀደ አሁን ባናውቅም፤ አዜብም ከባሏ ጋር እየገነነች በመጣችበት ዘመን ስለሷ እንዲወራ መፈለጉ ይገባናል።
እንግዲህ መለስ ዜናዊ እንዳለን አዜብ የራሷ ንግድ አላት፤ እሱን ካወቅነው ቆይተናል። ስብሃት ነጋን አባራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ያለውን ኤፈርትን ከመቆጣጠሯ በፊት የሜጋ አሳታሚ ሃላፊ እንደነበረችን እናውቃለን። ነገር ግን በግልጽ ከሚታወቁት የንግድ እንቅስቃሴዎቿ በተጨማሪ ጫት እና እንጀራ ሳይቀር ወደ ውጭ አገራት የመላክ ንግድ በማንቀሳቀስ እንደከበረችም መረጃዎች አሉ። እነዚህን የንግድ እንቅስቃሴዎቿን ከዳር ለማድረስም የመንግስት ተቋማትን እንዳሻት ስታሽከረክር ቆይታለች።
የቤተሰቡ የስራ ክፍፍል ግልጽ ሆኖ የቆየ ይመስላል፤ ባልየው የፖለቲካ ስልጣን ተቆጣጥሮ ጫት የሚያመላልሱላት ጄኔራሎች ያቀርብላታል፤ ከህግ በላይ ሆና የምትነግድበትን መንገድም ይፈጥርላታል። እሷ ከአስመጪ እና ላኪነት እስከ ችርቻሮ ድረስ ገብታ በመነገድ አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ለቤተሰቧ ከቢሊዮን ዶላር በላይ አከማችታለች።
አሁን አሁን ግን የቤተሰቡ ስራ አንድ ላይ ሰብሰብ እያለ ያለ ይመስላል። አዜብ ወደ ፖለቲካው አለም ገፍታ እየገባች ነው። የዛሬ አምስት አመት ፓርላማ በመግባት በንኡስ ኮሚቴ መሪነት ጀምራ፤ አሁን የህወሃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆናለች። ዳር ላይ ያሉ የንግድ ስራዎችን ትታም ኤፈርትን ተቆጣጥራለች። ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው እሁድ የዘገበው እና ዛሬ በዜና ክፍለ ጊዜ ያሰማናችሁ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ፥ መለስ ዜናዊ የአገሪቱ ዋና የስኳር ነጋዴ ለመሆን ትእዛዝ አስተላልፏል።
ጫት ቃሚዎች ሁሉ ከአሁን በኋላ በአረንጓዴው ቅጠል ስኳር ዘገን አድርጋችሁ ወደ አፋችሁ ስትጨምሩ፣ ቅጠሉንም ስኳሩንም የሰጣችሁን እያሰባችሁ ምርቃት ልታደርጉ እንደሚገባ ልብ በሉ። ወጣ ብላችሁ ለበርጫ የምትጠቱት ቢራም ቢሆን የሌላ አይደለም። ሰሜን ኮሪያውያን ለሚያገኙት መፍትሄ ሁሉ ምስጋና የሚገባው ለታላቁ መሪ፣ ለውዱ መሪ፣ ለጄኔራሉ እና ለአባታችን ኪም ጀንግ ነው እያሉ ፎቶግራፉን እጅ እንደሚነሱት፤ በቅርቡ የመለስ ዜናዊን ፎቶግራፍ ጎንበስ እያላችሁ መሳለማችሁ አይቀርም።
ገዢው ቤተሰብ የበርበሬ፣ የሽንኩርት እና የዘይትን ንግድ የተቆጣጠረ እለታ ደግሞ ምድረ ኢትዮጵያዊ የሚቀረው ቅሪት ቢኖር ትንፋሹ ብቻ ነው። የበርበሬ ነገር ከነተሳስ አይቀር አዜብ መስፍን እስካሁን ለምን እንዳላሰበችበት ሊገባን አልቻለም። ጣሊያን ኢትዮጵያን ለአምስት አመታት በተቆጣጠረ ጊዜ ወጥ ውስጥ ጨው አትጨምሩ ብሎ ህዝቡን ሊያሳብድ ምንም አልቀረው ነበር። አሁን ምድረ አበሻ በርበሬ ቢወሰድበት ጤናማ ሆኖ ይቀጥላል?
ወያኔ የማዳበሪያን ንግድ ተቆጣጥሮ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ገበሬ መሄጃ ባሳጣበት አስተሳሰቡ ስለ በርበሬ ያላሰበበት ምክንያት በእውነቱ ግልጽ አይደለም። ስሌቱ ቀላል ነው፦ በቃ፥ “የህዝቡን ጤንነት ለማሻሻል ሲል የኢትዮጵያ መንግስት ከአሁን ጀምሮ በርበሬ መመረት ያለበት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ነው ሲል መመሪያ አስተላልፏል። ከዚህ በኋላ በርበሬ የሚመረተው ከመንግስት ልዩ ፈቃድ በሚሰጣቸው ፋብሪካዎች ብቻ ነው። ፈቃድ ሳያገኝ በርበሬ ሲያመርት የተገኘ ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ በመሞከር ይከሰሳል፤ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞትም ይቀጣል።” የሚል አዋጅ ማውጣት።
ከዛ በኋላ በርበሬ የማምረት ፈቃድ ለኤፈርት መስጠት። ቀጥሎ በርበሬ ለመግዛት የሚፈልጉ ሁሉ በየቀበሌው እንዲመዘገቡ ትእዛዝ ማስተላለፍ። ያልተመዘገበ በርበሬ አያገኝም። ተመዝግቦ ዘግሞ ጸባዩን ያላሰመረም አይሸጥለትም። ገዢው ጸባዩን ባሳመረ ቁጥር የሚሸጥለት መጠን ከፍ ይላል፤ ባስከፋ ቁጥር ደግሞ እየቀነሰ ሄዶ ምንም እስካለማግኘት ይደርሳል።
የናንተን አናውቅም እንጂ ይሄ ለኛ ጥሩ የንግድ ሃሳብ ይመስለናል። ያለ ምንም ክፍያ ለቀዳማይ ነጋዴዋ ለማስተላለፍም ፈቃደኞች ነን። እንግዲህ በእውነቱ ይህ የተናገርነው ነገር ቀልድ ይምሰል እንጂ፤ የወያኔ አገዛዝ ባለፉት ሃያ አመታት ሲያካሄድ የቆየውን ዘረፋ ሂደት ከሞላ ጎደል የሚገልጽ ነው። ደግሞ እውነቱን በበርበሬ ላይ እንደዚህ ያለ መመሪያ ቢወጣ ሊገርመን አይገባም።
ሰዎቹ ላመኑበት ዘረፋ፣ ሌብነት እና ግድያ ጠንካሮች እና ጨካኞች ናቸው። ጥያቄው፥ እኛ ላመንበት እውነት፣ ፍትህ እና ነፃነት ምን ያህል ጠንካሮች እና ጨካኞች ነን የሚለው ነው።