በኢትዮጵያ የገንዘብ ተቋማት ዝርክርክነት እንደቀጠለ መሆኑ ተዘገበ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ሰነዶች፣ ሳይወራረዱና ሳይታረቁ በኢትዮጵያ ንግድ ዋናው መሥሪያ ቤት ሒሳብና የሒሳብ ማስታረቂያ መምሪያ ተወዝፈው እንደሚገኙ መታወቁን ኢሳት ባወጣው ዘገባ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እንደዘገበው አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶች በተለይም የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽንን የመሳሰሉ በርካታ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች፣ ሒሳባቸውን በወቅቱ የማያስታርቁ በመሆኑ ለአደጋ የተጋለጡ እንደሆኑ ሪፖርተርን ጠቅሶ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ዘገባው በሒሳብ ቁጥር ‹‹EIBO›› የቅርንጫፍ ሒሳብ ተብሎ በቅርንጫፍ መካከል የሚደረጉ የሰነድ ልውውጦች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ሒሳቦች በየጊዜው ሒሳባቸው ተሠርቶ የማይወራረድና የማይታረቅ በመሆኑ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሰነድ ሳይወራረድ በእንጥልጥል መገኘቱን አክሎ ዘግቧል፡፡
ኢሳት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅን ጠቅሶ እንደገለጸው 20 ሚሊዮን ብር በቅርንጫፋቸው ስም ተመዝግቦ የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ገንዘብ የቅርንጫፋቸው ዕዳ ይሁን ወይም ለቅርንጫፋቸው የተከፈለ ገንዘብ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ያልቻሉ መሆናቸውን መናገራቸውም አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይም በውጭ ምንዛሪ የሥራ ክፍል በርካታ የውጭ ምንዛሪ ሳይወራረድ ተከማችቶ ይገኛል ካለ በኋላ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የባንክ ባለሙያ እንደተናገሩት፣ ባንኩ በዓለም አቀፍ ኦዲተሮች ሒሳቡ እስካልተመረመረ ድረስ የፋይናንስ አቋሙን በትክክል መናገር አይቻልም ማለታቸውንም ኢሳት አክሎ ገልጿል፡፡
እንደ ኢሳት ዘገባ አብዛኛው የህወሀት ኩባንያዎች ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ እንደማይመልሱና ከባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ባንኩን አደጋ ላይ እየጣሉት መሆኑን መረጃ እንደደረሰው ገልጿል። እንደምንጮቹ ዘገባ ካልተወራረደው ከ20 ቢሊዮን ብር ውስጥ በርከት ያለው ገንዘብ የተያዘው በህወሀት ኩባንያዎች መሆኑንና ኩባንያዎቹ በጊዜው ብድራቸውን እንደማይመልሱ፣ ኪሳራ እንደማያስመዘግቡና እዳቸውን በምህረት እንደሚያሰርዙ፣ የክፍያ ጊዜ እንደሚያረዝሙ ገልጿል።