የወያኔ የ”እድገትና ትራንስፎርሜሽን” እቅድ ተብዬ ከመፈክርነት ያለፈ አይደለም ተባለ
የዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ካድሬዎች “እድገትና ትራንስፎርሜሽን” የተባለውን አዲስ “ቅኝት” ይዘው መነሳታቸው የአዲስ አበባን ህዝብ ከማስደንበር ባለፈ መልኩ ሊያታልለው እንዳልቻለ የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከመዲናይቱ ባስተላለፈው ዘገባ ገልጿል።
ዘጋቢያችንን ያናገሩት የመዲናይቱ ነዋሪዎች፥ “የከዚህ ቀደሞቹን ቅኝቶች ሰምተናቸዋል፤ አንዳቸውም መሻሻልን አላመጡም። ያለው እውነታ ድህነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት እና የመልካም አስተዳደር ጉድለት ነው ብለዋል።” በተያያዘ ዜናም፥ የአገዛዙ ካድሬዎች እና የመንግስት ሰራተኞች፣ በዚሁ “የእድገትና ትራንስፎርሜሽን” እቅድ ተብዬ ላይ ስልጠና ይውሰዱ በሚል በህዝብ ወጪ ወደ ፍቼ ከተማ እንደሚወሰዱ ለማወቅ ችለናል። ይህንንም በሚመለከት ለዘጋቢያችን አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች፣ ጊዜና የደሃውን ህዝብ ገንዘብ ከማባከን ውጪ ይህ የሚያመጣው ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በዩኒቲ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር የነበሩት ዶ/ር ታደሰ ብሩ፣ “ጯኺ መፈክሮች እና ውጤቶቻቸው” በሚል ርእስ በዚህ ሳምንት ባወጡት ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ “የመፈክር ኢኮኖሚ” ብለውታል። ዶ/ር ታደሰ፥ በአገራችን የነገሱት ተከታታይ አገዛዞች ኢኮኖሚውን በሚመለከት የፈጠሯቸውን መፈክሮች አስታውሰው፣ አንዳቸውም ግን ለውጥ እንዳላመጡ ጠቅሰዋል።
ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊም ባለፉት ሃያ አመታት ውስጥ የሰነዘራቸውን መፈክሮች ሲያስታውሱ፥ “በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን በቀን ሶስት ጊዜ ይበላሉ”፤ “ከእንግዲህ ከሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የጥይት ድምጽ የሚሰማው ለደስታ ብቻ ነው”፤ “ከአሁን በኋላ ሻማ የሚበራው ለልደት ነው” እና የመሳሰሉትን ንግግሮች ጠቅሰዋል። “ያልታደለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መፈክሮች ይቀያየሩበታል እንጂ እሱ ፍንክችም አይላት” ያሉት ዶ/ር ታደሰ፣ አዲሱ “የትራንስፎርሜሽን” እቅድ ተብዬም ካለፈው የተለየ እንደማይሆን ጠቁመዋል።