እዳር መቆም ይብቃን

ነፍሰ ገዳይ አገዛዞች የሚነግሱት ከዝምተኞች በተገነባ መሰረት ላይ ነው። እነሱ እንደ እሳት እየሰፉ ሲሄዱ ውሃ፣ አፈር፣ ቅጠል እና የተገኘውን ሁሉ በጊዜ አንስተው ተባብረው ወርውረው በማስቆም ፈንታ፤ ከዳር ቆመው “እኔን ምን አገባኝ” ከሚሉ ዝምተኞች። የአቋማቸውን ትክክለኛነት ለማስረገጥ፥ “ዝምታ ወርቅ ነው” የሚለውን የአባቶች አባባል ደጋግመው የሚጠቅሱ። ነገር ግን በዛው በተረተ አፋቸው ደግሞ፥ “እንዳው ዝም ማለት ለበግም አልበጃት፣ አስራ ሁለት ሆና አንድ ነብር ፈጃት” የሚለውን አባባል የሚዘነጉ ዝምተኞች። ጭጭ ባዮች፤ የነግ በኔ መርህ ጣሾች፤ የትብብር እንቅፋቶች፤ የጉርብትና ህግ ሰባሪዎች፤ አልቀው የሚያስጨርሱ የዋሆች።

ኢትዮጵያችንን ከዘረኞች ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ከሚሳተፉ የነፃነት ተጓዦች ጋር ጥቂት ንግግር ያደረገ ሰው፤ ቢያንስ ከአንድ የቤተሰብ አባል የ”አርፈህ ቁጭ በል” ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸው ይረዳል። ከጥቂት እድለኞች በስተቀር ብዙ ታጋዮች የቤተሰባቸውን ድጋፍ የላቸውም። የ”አርፈህ ተቀመጥን” ማስጠንቀቂያ ከሚያስተላልፉት የቤተሰብ አባላት ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ታጋዩ ከነፍሱ ጋር አጣብቆ የያዛቸውን የህይወት መርሆች ያስተማሩት ታላላቅ ወንድሞች ወይም ወላጆች ናቸው።

አትግደል፣ አትዋሽ፣ አትስረቅ፣ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፣ በጉረቤትህ ላይ አትቅና፣ ክፉን በሌሎች ላይ አትመኝ፣ መልካን አድርግ፣ ታላላቆችህን አክብር፣ የአይነ ስውሩን ሰው እጅ ይዘህ መንገድ አሻግር፣ ያለህ ለድሆች አካፍል፣ እና የመሳሰሉትን ብለው ያስተማሩ ወላጆች ወይም ታላላቅ ወንድሞች እና እህቶች መልሰው አይን ያወጣን ዘራፊ፣ ቀጣፊ፣ ዘረኛና አገር አጥፊ ቡድን አትዋጋ ሲሉ ግራ ያጋባል። “የት ነው ያለሁት ለመሆኑ? እውነት ይህ የኔው ወንድም ጋሼ ነው? እውነት ይህስ አባባ ነው? በምድር ላይ ነው ያለነው ውይስ አንድያችንን ሲኦል ወርደናል?” ያስብላል። የህልውና መሰረትንም ይነቀንቃል።

የወደዷት እና ያፈቀሯት ዘረኞችን በመታገል ህይወቴን ላደጋ አጋልጠሃል ብላ ጀርባ ስትሰጥ፥ ትክክለኛነትን መጠራጠርም ይመጣል። “እኔ እሆን የተሳሳትኩት?” ብሎ መጠየቅም አለ። በሌላ መንገድ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ ካላቸው ፍላጎት በስተቀር ታጋዩ በወሰደው አቋም ላይ አንድም ምክንያታዊ የሆነ ተቃውሞ እንደሌላቸው ሲታወቅ ሌላ የሚፈጥራቸው ስሜቶች አሉ። ከነዚህም አንዱ የንቀት ስሜት ነው። ለልባችን ቅርብ የሆኑ ሰዎች ጠንካሮች እና መመኪያዎች ሆነው ብናያቸው የሁላችንም ምኞት ነውና፤ ተራ ፈሪዎች ሆነው ሲገኙ ግን ሳንወድ በግድ እንንቃቸዋለን። ይህ ንቀት ደግሞ ከፍቅራችን ጋር አብሮ አልሄድ እያለ መላ ቅጡ የጠፋው ሁኔታ ውስጥ ይከተናል።

ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች መቼም ጊዜያዊ መቆራረጥ ቢከሰት እንኳ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ቀን ተመልሰው ይመጣሉ። ብዙ ትዳሮች ግን ፈርሰዋል፤ ወደፊትም ትግሉ እየመረረ እና እየጎመዘዘ ሲሄድ፤ መንፈሰ-ጠንካራ የሆኑት ታጋዮች በእምነታቸው ላይ ሙጭጭ ብለው አልለቅ ሲሉ፤ መፍረሳቸውን ይቀጥላሉ። ጓደኝነቶችም ተሰብረዋል፤ መሰበራቸውንም ይቀጥላሉ። ይህ የአብዛኞቻችን የለት ተለት እውነታ ነው፤ አዲስ ነገር አይደለም።

በዛሬው የዜና ክፍለ ጊዜ ያሰማናቸው ወሬዎች በሙሉ ኢትዮጵያችንን በጉልበት ተቆጣጥሮ ያለውን ዘረኛ አገዛዝ እኩይ ባህሪያት የሚገልጹ ናቸው። በየዜናው የምናሰማችሁ የዘረኝነት፣ የዘረፋ እና የቅጥፈት ወሬ እኛን እንደሚያንገፈግፈን እና እንደሚያቅለሸልሸን ዝምተኞቹን አለመሰማቱ ሁሌም ቢሆን የሚገርመን ነው፤ ለዛሬው ትንታኔ መነሻ የሆነንም ይኸው መገረም ነው።

ሰዎች ድህነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ አምባገነናዊነት እና ዘረኛነት የነገሰባትን አገር ያለምንም ሃፍረት እና መጨነቅ ለልጆቻቸው ሲያወርሱ ማየት ለአንዳንዶቻችን ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው። ልጆቻቸው ቢሞቱ ወይም አንድ አደጋ ላይ ቢወድቁ ጨርቃቸውን ጥለው የሚጮኹ እና የሚያለቅሱ ወላጆች ነፍሰ-ገዳይ የሆነን አገዛዝ በዝምታ ለልጆቻቸው ማውረሳቸው እርስ በርሱ የሚጣረስ ጉዳይ አይደለምን?

እንግዲህ በመከራ ማለፍ፣ መገፋት፣ እና በእሳት መፈተን ለጊዜው የሚጎዳውን ያህል ዘላቂ ጥቅም እንደሚኖረው ታጋዮቹ ሊያውቁ ይገባል። ስንዴው ከእንክርዳዱ የሚለየው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ከምንም በላይ ግን፥ ታጋዮች አቋማቸውን የሚመዝኑት በሌሎች ግለሰቦች ስሜት ላይ ተመስርተው ሊሆን አይገባም። ሰዎች ይነሳሉ፣ ይወድቃሉም። ቢያንስ በዚህ ምድር ላይ እንደ ሃሳብ ዘላለማዊ አይደሉም። በወዳቂ ነገር ላይ እራስን ማቆም ደግሞ ሞኝነት ነው።

የሰው ልጅ እንደ ሰውነቱ ሊያገኘው የሚችለውን ክብር የሚያሰጡት፤ ከመቃብር ያለፈ ህይወት የሚያስገኙለት፣ ስጋና ደሙ አይደሉም። ስጋና ደም አፈር ውስጥ ከገቡ በኋላ መልሰው አይገኙም፤ ብንን ብለው ይጠፋሉ። ሰውን የሚያስከብረው በህይወት ሳለ የኖረለት፣ የተጋደለለት እና ከነፍሱ ጋር ያስተሳሰረው ሃሳብ ነው። ዘላለማዊነትን የሚሰጠውም ይኸው ነው። እንግዲህ የነፃነት ተጓዦች በዚህ እየተጽናኑ ጉዟቸውን ይቀጥሉ። ለዝምተኞችም ቢሆን፣ ሃሳብ ለመለወጥ፣ ከአላፊ ስጋና ደምነት አልፎ ዘላለማዊ ከሆነው ትግል ለመቀላቀል ጊዜው መቼም ቢሆን አይረፍድምና ተነስታችሁ ዘረኛነትን ታገሉ እንላለን።