የቂርቆስ ክፍለከተማ ከ150 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ጠርቶ አካባቢያቸውን በአስቸኳይ እንዲለቁ ትእዛዝ ሰጠ፣ ነዋሪዎቹ በውሳኔው ማዘናቸውን ገልጸዋል
የቂርቆስ ክፍለከተማ ባለስልጣናት በወረዳ 18 ቀበሌ 27 ወይም ሜጋ ህንጻ ፊት ለፊት የሚኖሩ የ157 ቤት ባለቤቶችን ጠርተው ቪላ ቤቶችን አፍርሰው ባለ 4 ፎቅ ህንጻ እንዲሰሩ የማይሰሩ ከሆነ ግን በሁለት ወራት ውስጥ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ወይም መንግስት በሚሰጣቸው የኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ እንዲገቡ ትእዛዝ ሰጥቷል።
በመንግስት ድንገተኛ ትእዛዝ የተደናገጡት ነዋሪዎች ለዘመናት የኖርንበትን አካባቢ በሁለት ወራት ውስጥ ልቀቁ ስንባል በእጅጉ አዝነናል ሲሉ ማማረራቸውን ኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢውን ጠቅሶ ዘግቦአል ።
በአካባቢው የሚገኙት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው ሳለ አፍርሱ መባሉ አልተዋጠልንም የሚሉት ነዋሪዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰሩትን የሚአውቁ አልመስለን ብሎአል ሲሉ ተችተዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ከሪል ስቴት ልማት ጋር በተያያዘ ተፈጠረ ላለው ሕገወጥ ተግባር፣ በሕግ መጠየቅ አለባቸው ያላቸውን አልሚዎችና በቀድሞ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን መረጃ እየሰበሰበ መሆኑን ሪፖርተር የተባለው ለሥር ዓቱ ቅርበት ያለው ጋዜጣ ዘግቧል።
መረጃዎች ተተንትነው ከተጠናቀሩ በኋላ አስተዳደሩ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን አልሚዎችና ሠራተኞች ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስድ ታውቋል።
ሕገወጥ ናቸው የተባሉት አልሚዎች ካለፈው ወር ጀምሮ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱት በአስተዳደሩ የከፋ ‹‹ወንጀል›› ፈጽመዋል የሚባሉት እንደሆኑ ጋዜጣው ዘግቧል።
አንዳንድ አልሚዎች በሊዝ ቦርድ ከተወሰነላቸው በተጨማሪ ከመሬት ባለሥልጣን ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር የማይገባቸውን ቦታ ወስደው ግንባታ ማካሄዳቸውን፣ በዚህም መንግሥት ማግኘት የነበረበትን ገቢ እንዲያጣ አድርገዋል ያላቸውን አልሚዎች፣ በሕገ መንግሥቱ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ተብሎ ቢደነገግም፣ ግንባታ ሳያካሂዱ መሬት በመሸጥ የማይገባቸውን ጥቅም በማግኘታቸው አስተዳደሩ በሕግ ከመጠየቅ ወደኋላ እንደማይል ተመልክቷል።
አስተዳደሩ ከዚህ በተጨማሪም ለሪል ስቴት ልማት በወሰዱት ቦታ ላይ የፕሮግራም ለውጥ ባደረጉ፣ የአገልግሎት ለውጥ ባደረጉ፣ በሕገወጥ መንገድ አስፋፍተው በያዙት ቦታ ላይ ግንባታ ባካሄዱ፣ የተሰጣቸውን ቦታ ለሦስተኛ ወገን ባስተላለፉ፣ ያለግንባታ ፈቃድ የገነቡ አልሚዎች በሙሉ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
እነዚህ አልሚዎች ባጠፉት ጥፋት መሠረት የአካባቢውን ከፍተኛ የሊዝ ጨረታ ዋጋ እንዲከፍሉ አስተዳደሩ ወስኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግብረ ኃይሉ ጥፋተኛ ያላቸውን አልሚዎች ያሉበትን አካባቢ ከፍተኛ የሊዝ ጨረታ ዋጋን በማጥናት ላይ መሆኑን ከጋዜጣው ዘገባ ለመረዳት ይቻላል።
ክፍያውን ለመክፈል ፈቃደኛ የማይሆኑ አልሚዎችን ካርታቸውን እንደሚያመክን፣ በሕግ እንደሚጠይጠቃቸውና ያለፈቃድ የተገነባውንም ግንባታ እንደሚያፈርስ ግብረ ኃይሉ ወስኗል፡፡
በከተማው አስተዳደር በ141 አካባቢዎች 125 አልሚዎች ስድስት ማሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ለሪል ስቴት አልሚዎች የተሰጠ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሪል ስቴት አልሚዎች በሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ።
አልሚዎቹ የአስተዳደሩ ዕርምጃ ግብታዊ ነው፤ ሕግን የተከተለ አይደለም በሚል መቃወማቸውን ቢቀጥሉም፣ በአስካሁኑ ሒደት ተቃውሞቸው ተሰሚነት እንዳጣ መረዳት ችለናል ሲል ጋዜጣው ገልጿል።
ብዙዎች መስተዳድሩ እየወሰደው ያለውን እርምጃ ቢደግፉም፣ ጥቃቱ በእወነተኛ ባለሀብቶች ላይ የተሰነዘረ እንጅ ከመንግስት ጋር በሞሞዳሞድ ያለአግባብ በከበሩትና በመንገስት ባለስልጣናት ላይ አለመሆኑንም ጋዜጣው ገልጸዋል።
የወያኔ መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችና ሚኒሰትሮች በቦሌ መድሀኒአለም አካባቢ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቤቶችን ከህዝብ በዘረፉት ሃብትና ንብረት መገንባታቸው ይታወቃል።