በቅዱስ ዮሴፍ መቃብር ያረፉ አጽሞች መረበሽ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ታሪካዊው የቅዱስ ዮሴፍ መቃብር አርፈው የሚገኙ በሺሆች የሚቆጠሩ አጽሞች ተቆፍረው እየወጡ እና በጅምላ መቃብሮች ውስጥ እየተቀበሩ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።
አዲስ ፎርቹን የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ እንደዘገበው፥ ባለፈው አመት የተመሰረተው እና የአዲስ አበባ ቋሚ የቀብር ቦታ ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የተባለው ድርጅት እስካሁን ሁለት ሺህ መቃብሮችን ቆፍሮ አብዛኞቹን አጽሞች ወደ ጅምላ መቃብሮች አስተላልፏል። በተጨማሪ አራት ሺህ መቃብሮችን የመቆፈሩ ስራም እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ላለፉት ሃምሳ አመታት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው እና የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት የሆነው ቅዱስ ዮሴፍ መቃብር በ12.3 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ላለፉት ሁለት አመታት መሙላቱ እየታወቀ ቀብር ሲካሄድበት መቆየቱም ታውቋል።
አዲሱ ኤጀንሲ መቃብሮቹን መቆፈር እንደሚጀምር በተለያዩ ሚድያዎች፣ በእድሮች እና በሰንበቴዎች አማካኝነት መልክት ማስተላለፉን ቢናገርም፤ ይህንን ማስታወቂያ ሰምተው የየዘመዶቻቸውን አጽም ሊረከቡ የመጡ ቤተሰቦች ቁጥር በጣም ትንሽ እንደሆነ ግን አምኗል። ቤተሰቦቻቸው ያልመጡላቸው አጽሞችም ኤጀንሲው ወደቆፈራቸው የጅምላ መቃብሮች እየተዛወሩ እንደሆነ ታውቋል።
አዲስ ፎርቹን በዘገባው አጽሞቹን አስወጥቶ እንደገና ማስቀበር በርካታ ሺህ ብር የሚያስወጣ ሂደት እንደሆነና ለብዙ ቤተሰቦች የማይቀመስ መሆኑን አመልክቷል።
የዘመዶቻችሁን አጽም ኑና ውሰዱ በመባላቸው ካዘኑ ሰዎች መልክት ደርሶኛል ያለው ኢትዮጵያን ሪቪው ድረ-ገጽ፣ አዲስ አበባ በብዙ አቅጣጫዎች ማደግ የምትችል ከተማ ሆና ሳለች የወያኔ አገዛዝ በሺዎች የሚቆጠሩን የሟቾች ቤተሰቦች ለዚህ አይነት እንግልት ለምን እንደሚዳርግ ግልጽ አይደለም ብሏል።
ለዝግጅት ክፍላችን መልክት የላኩ ኢትዮጵያዊ የግንቦት 7 ሬድዮ እንደዚህ ባለ አስፈላጊ ርእስ ላይ ዘገባ አለማቅረቡ እንዳሳዘናቸው የገለጹ ሲሆን፤ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላ ግለሰብ ደግሞ በወያኔ ሹሞች የሚመራውን የአዲስ አበባ መስተዳደር ስራ “እርኩሰት” ብለውታል።