የኦፌዴን ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባል ለስደት መዳረጋቸው ታወቀ

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ (ወይም ኦፌዴን) የስራ አስፈጻሚ አባል እና የሶሾ-ኢኮኖሚክ ደፓርትመንት ሃላፊ የነበሩት ዶ/ር ታመነ ለታ ለስደት መዳረጋቸውን “ኦሮሞ ፓርላመንታሪያንስ” የተባለ ድረ-ገጽ ዘግቧል።

ከድረ-ገጹ ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉት ዶ/ር ታመነ ለምን እንደተሰደዱ ሲገልጹ፦ ምንም እንኳ የህጋዊ ፓርቲ አባል ቢሆኑም ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የኦነግ አባል ነህ ብሎ እንደከሰሳቸው፤ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ከስራ እንደተባረሩ እና በግል ተቋማት ስራ ለመያዝ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ከአገዛዙ ጣልቃ ገብነት የተነሳ እንዳልተሳኩ ተናግረዋል። በኔ፣ በቤተሰቤ እና በዘመዶቼ ላይ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ይደረግ ነበር ያሉት ስደተኛ፤ ባልታወቀ ግለሰብ በገዛ ግቢያቸው ከመደብደብ አንስቶ ወደ ሰዋራ ስፍራ ተወስደው ሰቆቃን እስከመቅመስ ድረስ የደረሰባቸውን ግፍ ዘርዝረዋል።

የወያኔ አገዛዝ ህብረ-ፓርቲ ስርአት እየገነባሁ ነው ብሎ እንደሚያወራ፤ በተግባር ግን የአንድ ፓርቲ ስርአት ሲገነባ እንደቆየ፤ እንዲሁም የጅምላ እስር እና አፈና እንደቀጠሉ አስረድተዋል።

ዶ/ር ታመነ ባለፉት አራት አመታት ከተሰደዱ የኦፌዴን አባላት ውስጥ ስምንተኛው መሆናቸውን ድረ-ገጹ ዘግቧል። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2009፣ ከ42 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በአለም ዙሪያ ባሉ አገራት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን መግለጹን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።