ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ እርዳታን ለጭቆና እያዋለ ነው ሲል ሂውማን ራይትስ ዋች አወገዘ
ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን “ሂውማን ራይትስ ዋች” ማክሰኞ እለት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያውያን ስም ከምእራባውያን አገራት የሚሰበሰበው እርዳታ ለጭቆና እየዋለ ነው ሲል በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ወቀሳን ሰንዝሯል።
አንድ መቶ አምስት ገጾች ያሉት እና “እድገት ያለነጻነት፡ እርዳታ በኢትዮጵያ ጭቆናን ሲደግፍ” የሚል ርእስ ያለው ሪፖርት የወያኔ አገዛዝ ከምእራባውያን የሚሰበስበውን እርዳታ ዜጎችን ለመቆጣጠር እና ስልጣኑን ለማጠናከር እንደሚጠቀም መስክሯል።
አገዛዙ የማይደግፉትን ዜጎች አለአግባብ እርዳታ እየነሳ ነው የሚለው ሪፖርት፤ ይህ እየሆነ ግን ምእራባውያን አገራት እንዳውም የሚሰጡትን ገንዘብ እየጨመሩ ነው ብሏል። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2008፣ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያውያን ስም ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱ እና የአውሮፓ ህብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ፣ እና ጀርመን ዋናዎቹ ለጋሾች እንደሆኑም ታውቋል።
ገለልተኛ ጥናት ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም በሶስት ክልሎች ውስጥ ከሁለት መቶ በላይ ዜጎችን ለማነጋገር የቻለው ሂውማን ራይትስ ዋች፤ ዘረኛው አገዛዝ የተራቡ ልጆች ያላቸውን ገበሬዎች ሳይቀር የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ናችሁ በሚል እርዳታ ሲከለክል እንደቆየ አጋልጧል። ኢትዮጵያውያን ማዳበሪያ ለማግኘት፣ በሴፍቲ ኔት ለመሳተፍ እና አስቸኳይ እርዳታ ለመቀበል፤ እንዲሁም ስራ እና የትምህርት እድል ለማግኘት የገዢው ቡድን አባል ሁኑ በሚል እየተገደዱ መሆኑን ሪፖርቱ ዘርዝሯል።
ሂውማን ራይትስ ዋችን በድብቅ ያናገሩ የለጋሽ አገራት ተወካዮች ይህ ችግር እንዳለ ቢያምኑም፤ በግልጽ ግን ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም።
ድርጅቱ ለጋሽ አገራት ገንዘባቸው ለጭቆና መዋሉን እንዲያቆም ለማረጋገጥ እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል። ይሁን እንጂ በተለይ በኢትዮጵያ ያሉ የአለም ባንክ ሰራተኞች ምናልባት በ20 አመታት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር፣ ዴሞክራሲ በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ አስፈላጊ አይደለም ማለታቸው ተጠቅሷል።