አምና እንዴት አለፈ፤ ለዘንድሮስ ምን ሰነቅን?

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገረን ይላል።

ያለፈው ዓመት ለኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች የመከራ ዓመት ነበር። በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬት ለባዕዳን ተቸብችቧል። ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ከአራት አስርት ዓመታት በፊት “መሬት ላራሹ” የሚል መፈክር አንግበው ሕይወታቸውን የሰውት የኢትዮጵያ መሬት በኢትዮጵያዊያን ጉልተኞች ተይዞ ገበሬው “አርሰህ ሲሶ ገብር” ስለተባለ ነበር። ዛሬ ግን የኢትዮጵያ መሬት በባዕዳን ጉልተኞች ተይዞ ገበሬው ሙሉ በሙሉ ከግብርናው ተነቅሎ “የቀን ሠራተኛ ሁን” እየተባለ ነው። “ከድጡ ወደ ማጡ” የተባለው በኢትዮጵያ አርሶ አደር ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያዊያን ከተሞች የቅኝ ግዛት ከተሞች ሆነዋል። ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው በአደጉ አገሮች እንኳን የማይገኙ የተንጣለሉ ቤቶችና ግቢዎችን ሲገነቡ ድሃው ከደሳሳው ጎጆው እየተፈናቀለ መውደቂያ አጥቷል። ባሳለፍነው ዓመት አዲስ አበባ ከፍተኛ የሃብት መበላለጥ የሚታይባት አፍሪካዊት ከተማ ሆናለች።

ኑሮ እየከፋ ቢሆንም ወያኔን ሕዝቡን በወሬ እንዳጠገበው ነው። “አብዮታዊ ዲሞክራሲ”፣ “ቦናፓርቲዝም”፣ “ጥገኛነት”፣ “ልማታዊነት፣ “ኒዮ ሊበራሊዝም” … እነዚህ ሁሉ የወያኔ ማምታቻ ቃላት ናቸው። 2002 ሲገባደድ ደግሞ “ትራንስፎርሜሽን” የተሰኘ አዲስ ማምታቻ ይዞ መጥቷል። በዚህ አዲስ ማምታቻ ሕዝቡን የተስፋ እንጀራ ይቀልባል።

2002 ያለፈው እስር ቤቶች በነፃነት ታጋዮች እንደተሞሉ ነው። ለራሱ ክብር የሚሰጥ፣ ለነፃነቱ ቀናኒ የሆነ እና ሃገሩን የሚወድ ዜጋ መኖሪያው እስር ቤት የሆነባት አገር ኢትዮጵያ ነች። የዛሬይቷ ኢትዮጵያ በህፃናትና አዛውንት እስረኞች ላይ ሰቆቃ የሚፈፀምባት አገር ናት።

ያለፈው ዓመት የወያኔ ዘረኝነት “ከወርቅ ሕዝብ” ወደ “ወርቅ ጎጥ” ከዚያም ወደ “ወርቅ ቤተሰብ” በመጨረሻም ወደ “ወርቅ ግለሰብ” የዘቀጠበት ዓመት ነበር። የዚህ የቁልቁለት ጉዞ ከዚህ በታች መወረድ እማይችልበት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ በቅርቡ በተደረገው የወያኔ ጉባዬ ውጤት ተረጋግጧል። የአገዛዙ እምብርት የሆነው ወያኔ አመራር በመለስና ስብሃት የሥጋና የጋብቻ ዘመዶች እንዲያዝ ተደርጓል። በአንፃሩ ደግሞ በየክልሉ የተደራጁት ሎሌ ድርጅቶች መሪዎች እንደካርታ ተፐዋውዘው ቦታ እንዲቀያየሩ ተደርጓል። በዚህም የመለስ ዜናዊ ቤተሰብ በህዋህት ውስጥ ሲደላደል በየክልሉ ባሉ ሎሌ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት ግንባር ቀደም አገልጋዮች ምቾች እንዳይሰማቸው ተደርጓል። ይህም የዘረኝነት አለንጋ ራሳቸው ወያኔዎችንም ጭምር እየገሸለጣቸው መሆኑን ያሳያል።

2002 መለስ ዜናዊ እንደ ቪኦኤ አይነቱን የውጭ አገራት ዜናዎችን እንደሚያፍን በግልጽ የተናገረበት ዓመት ነው። እውነተኛ መረጃን ነፍጎ በምርኮ የያዘውን ሕዝብ በጨለማ እየነዳ ነው።

ባጭሩ ያለፈው ዓመት የወያኔ ፋሽስትነት ፈጦ የወጣበት፤ ዘረኝነት የሁላችንም የጋራ ጠላት መሆኑ በማያሻማ ሁኔታ የተረጋገጠበት ዓመት ሆኗል።

ባለፈው ዓመት ለነፃነት በሚደረገው ትግል ጎራም የተፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች አሉ። ከሁሉም በፊት ወያኔ ለሰላማዊ ትግል ያለውን እድል ሙሉ በሙሉ የዘጋ በመሆኑ “ወያኔን በምን መንገድ እንታገለው?” የሚለው ጥያቄ አላስፈላጊ ሆኗል። ከወያኔ በኋላ በምትኖረው ኢትዮጵያ ባህርያትም ላይ ወደ መግባባት እየተሄደ ነው። በተፈለገው መንገድ ባይፈጥንም እንኳን ይህ ሂደት የነፃነት ኃይሎችን አስተባብሯል። ዛሬ ብዙዎች ከወያኔ በኋላ የምትኖረውን በየደረጃው በሕዝብ ነፃ ፈቃድ በተመረጠ መንግሥት የምትመራን ውብ አገር አሻግረው መመልከት ችለዋል። በዚህም ምክንያት በድርጅቶች መካከል የነበረው ሽኩቻ እየቀነሰ፤ ተቀራርቦ የመሥራት ባህል ደግሞ ከእለት ወደ እለት እየጎለበተ መጥቷል። እጅግ ብዙ ቢቀረንም አበረታች ምልክቶች እየታዩ ነው።

በሲቪሉ ማኅበረሰብም ውስጥ “የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል” የሚለው እምነት ከመጎልበትም አልፎ በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተተረጎመ ነው። የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ጥምረት መፈጠሩ የዚህ ውጤት ነው።

የኢሳት ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) መፈጠርም ኢትዮጵያዊያን በኅብረት ከተነሱ እንደምን ያለ ውጤቶችን ሊያመጡ እንደሚችሉ ያመላከተ ነው።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያለፈውን የትግል ዘመን ያሳለፈው ድርጅታዊ ብቃቱን በማጎልበት ነበር። ዛሬ ግንቦት 7 በኢትዮጵያም ከኢትዮጵያ ውጪም ጠንካራ ድርጅታዊ መሠረት ተክሏል፤ ከሌሎች የፓለቲካና የሲቪክ ማኅበራት ጋር ያለውንም ግኑኝነት አዳብራል። በቅርቡም ከሁለት ኢትዮጵያዊያን የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጥሯል።

ከሌሎች ድርጅቶች ጋር መተባበራችን የወያኔን ውድቀት ማፋጠን ብቻ ሳይሆን የወደፊቷን ኢትዮጵያ መሠረት መጣል ነው ብለን በጽኑ እናምናለን።

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች በጋራ ተነስተን ወያኔን የምናርበደብድበት ይሆናል ብለን እናምናለን። ለዚህም ቀንና ለሊት በትጋት እንሰራለን።

2003 ዓም የፍሬዓማ ትግል ዓመት እንዲሆንል እንመኛለን።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!