አዜብ መስፍን የህወሃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና መሾሟ ተዘገበ

የዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ባለቤት የሆነችው አዜብ መስፍን በህወሃት አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና መሾሟ ተዘግቧል።

በኢትዮጵያ ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው ቡድን አስኳል የሆነው ህወሃት (ወይም ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ሐሙስ እለት አስረኛ መደበኛ ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ ስምንት የቀድሞ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱንም አሰናብቷል። ከስምንቱ ውስጥ፥ የፓርቲው አባት እና የመለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ሞግዚት እንደሆነ የሚነገርለት ስብሃት ነጋ በእርጅና ስም መልቀቂያ ጠይቋል ሲል የአገዛዙ አንደበት የሆነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ዘግቧል።

ስብሃት ነጋ ከዚህ ቀደም ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነቱ እንደተወገደ ይታወሳል። ከዛሬ አመት በፊት በአሜሪካ ድምጽ ራድዮ የአማርኛ ዝግጅት ላይ ለቃለመጠይቅ ቀርቦ ጉዳዩን በሚመለከት ጥያቄ የቀረበለት ስብሃት፣ “በፓርቲው አካባቢ እሱን ያለመፈለግ ሁኔታ” እንዳለ ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች የስብሃት ከቁልፍ የስልጣን መቀመጫዎች መወገድ ከአዜብ መስፍን ጋር ሳይያያዝ እንደማይቀር ይናገራሉ።

የዘረኛው አምባገነን ባለቤት ከተወሰኑ አመታት ወዲህ እየገነነች የመጣች ሲሆን፤ በፓርቲው ውስጥ ከስብሃት ነጋ ጋር በከረረ የግል ሽኩቻ ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል። ስብሃት ነጋ የወያኔ ኩባንያ የሆነውን ኤፈርትን ከማስተዳደር ስራው ሲነሳ አዜብ መስፍን የምክትልነት ካባ ለብሳ ድርጅቱን መቆጣጠርዋ ይታወቃል።

በዚሁ የህወሃት አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ስዩም መስፍን፣ አርከበ እቁባይና አባይ ጸሃዬ ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ተነስተዋል። በተያያዘ ዜና፥ የወያኔ ተለጣፊ ፓርቲ የሆነው ብአዴን (ወይም ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) የረዥም ጊዜ የይስሙላ መሪው የነበረውን አዲሱ ለገሰን አስወግዶ በደመቀ መኮንን ተክቶታል። ሌላኛው ተለጣፊ ፓርቲ ኦህዴድ አባ ዱላ ገመዳን አስወግዶ አለማየሁ ቱምሳን በሊቀመንበርነት ተክቶታል።