ኢሳት አፈና ተቋቁሞ በአየር ተመለሰ

ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ከህዳር 23 2003 ዓም ጀምሮ ላለፉት ሁለት ወራት ስርጭቱን በታይኮም 5 ሲያስተላለፍ መቆየቱ ይታወሳል። በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ይህን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማፈን ያለፉትን ሁለት ወራት ላይ ታች በማለት አሳልፎአል። ገዢው ፓርቲ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሦስት ሚሊዮን ህዝብ ለከፍተኛ የረሀብ አደጋ በተጋለጠበጥ ወቅት፣ በድሀ ህዝብ ሥም በልመና የተገኘን የውጭ ምንዛሪ፣ ኢሳትን ለማፈን ተግባር እንዲባክን አድርጎታል።

የኢሳት ልጆችና የኢሳት ደጋፊዎች አስቀድሞ ከራሱ ከመንግስት ባለስልጣናት በደረሳቸው መረጃ መሰረት አማራጭ የመውጫ መንገዶችን ሲፈልጉ ከርመዋል። በኢሳት ልጆች ጥረት ሙከራው ተሳክቶ በ24 ሰአት ውስጥ ያን መተንፈሻ ያጣ ህዝብ መተንፈሻ ቀዳዳ ሊሆኑት እንደገና በኢንቴል ሳት 10 (Intelsat 10 at 68.5 East ፣ CBand፣ Transponder 14፣ Downlink: 3808 V፣ Symbol rate: 10340 ፣ FEC: ¾) ስርጭት መልሶ ጀምሯል።

በዚህ አጭር ጊዜ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ በሺ የሚቆጠሩ የስልክ መልእክቶች ደርሰውናል። ሁሉም መልእክቶች በርትተን እንድንሰራ፣ በሁለትና በሶስት የማሰራጫ ጣቢያዎች ስርጭታችንን እንድናስተላልፍ የሚጠይቁ ናቸው።

አሁን ከአጭር ቀናት መቋረጥ በሁዋላ ተመልሰን መምጣታችን ለእኛ እንደታላቅ ድል ሊቆጠርልን ይችል ይሆናል። ያ ግን አይደለም። ይህ ድል የእኛ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ድል ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ይዞ የተሸነፈ ሀይል የለም። ታሪክ ምስክር ነውና።

አሁንም ድላችን ገና ነው። የድላችንን ሻማ የምናበራው የፕሬስና ሌሎች ነጻነቶች በአገራችን ሰፍነው ስናይ ብቻ ነው። ይህ እስከሚሆን ድረስ እየወደቅን እየተነሳን ትግላችን እንቀጥላለን።