ወያኔ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ ሽግሽግ ሊያደርግ ነው

ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ ሽግሽግ ለማድረግ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀና ስዩም መስፍንም ከሚኒስትርነቱ እንደሚነሳ ለአገዛዙ ቅርበት ያላቸው የዜና ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ስዩም መስፍን ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት ሲሰራ እንዳለ ይታወቃል። ምንጮቻችን እንዳስተላለፉት መረጃ፥ አዲሱ ፓርላማ በቅርቡ ስብሰባውን ሲጀምር ላለፉት 20 ዓመታት በምክትል ሚንስትርነት ሲያገለግል የነበረው ተቀዳ አለሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መቀመጫውን ይረከባል። ከሚኒስቴርነቱ የሚነሳው ስዩም መስፍን ደግሞ በአሜሪካ የወያኔ አምባሳደር ሆኖ እንደሚሾም ለማወቅ ተችሏል።

ስዩም ከሚኒስቴርነቱ ተጨማሪ የተለያዩ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ የሰራ ሲሆን፤ በስራ ዘመኑም የዘረኛውን አገዛዝ አጀንዳ ሲያስፋፋ እንደቆየ ይነገራል። ስዬ አብረሃ ስልጣን ከለቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢ የሆነው ስዩም፣ ተቋሙ በትግራይ ተወላጆች እንዲሞላ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርግ እንደቆየ እና በቅርቡም የድርጅቱን ስራ አስኪያጅ ግርማ ዋቄን አባሮ በተወልደ ገብረማርያም መተካቱ ይታወሳል። እንደ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ቦርድ ሰብሳቢም፣ የወያኔ ኩባንያዎች የሲሚንቶ ፋብሪካውን ገበያ እንዲቆጣጠሩት መንገድ ለመጥረግ የመንግስት ንብረት የሆነውን ድርጅት የማዳከም ስራ ሲሰራ እንደቆየ አንዳንድ ምንጮች ይገልፃሉ።

መረጃውን ለዝግጅት ክፍላችን የላኩት ምንጮች እንዳስረዱት፥ የስዩም መስፍን የአምባሳደርነት ሹመት መንታ አላማ ያዘለ ነው። ወያኔ ሳሙኤል አሰፋን ከሻረ በኋላ ተዋህደ በላይ የተባለን ግለሰብ አሜሪካ በሚገኘው ኤምባሲ እንደ ዋና ዲፕሎማት እንዲሰራ ቢልከውም፤ ግለሰቡ እየተበላሸ የሄደውን የአሜሪካና የወያኔ ግንኙነት ሊያሻሽል እንዳልቻለ ጠቁመዋል። በዚህ ተስፋ የቆረጠው አገዛዝም ስዩም መስፍንን እንደ መጨረሻ መሳሪያ ለመጠቀም ማሰቡን ለማወቅ ተችሏል።

እንደ ምንጮቻችን ገለፃ፥ የስዩም ወደ አሜሪካ መላክ ሁለተኛ አላማ የአገዛዙ ባለስልጣናት ገንዘብ ከአገሪቱ እየዘረፉ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለማሸሽ ለሚያደርጉት ዘመቻ ሽፋን እንዲሰጥ እና እንዲያጠናክር ነው። ከዚህ ቀደም በአሜሪካ የወያኔ አምባሳደር ሆኖ ይሰራ የነበረው ብርሃነ ገብረክርስቶስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንቀሳቅስ እንደነበረና ከሚስቱ ጋር ተጣልቶ ወደ ፍርድ ቤት ክርክር ሲገባ እንደተጋለጠ ይታወቃል። ብርሃነ በወቅቱ ገንዘቡ የሱ ሳይሆን የመለስ ዜናዊ እንደሆነ መግለጹንም ምንጮች ይናገራሉ።

የተቀዳ አለሙን ሹመት አስመልክቶ አስተያየት የሰጡን የፖለቲካ ተንታኝ፥ ወያኔ የተወሰኑ ኦሮሞዎችን ወይም አማሮችን ከፊት ለፊት አስቀምጦ ከበስተጀርባቸው እውነተኛውን ስልጣን የያዙትን እና “ታኮ” በመባል የሚታወቁትን የትግራይ ተወላጆች የማስቀመጥ ልምድ እንዳለው በማስታወስ፤ ተቀዳ አለሙ ከምልክትነት የበለጠ ስልጣን እምደማይኖረው አስረድተዋል።