የማህበራት ካፒታል በንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንዲንቀሳቀስ የወያኔ አገዛዝ መመሪያ ማስተላለፉ ታወቀ
ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ከዚህ በኋላ ማንኛቸውም በማህበር የተደራጁ ተቋማት ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ገንዘባቸውን በንግድ ባንክ በኩል እንዲያንቀሳቅሱ የሚል መመሪያ በነሐሴ ወር መጨረሻ 2002 ማስተላለፉን የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ከሰሜን ኢትዮጵያ ባስተላለፈው ዘገባ አስታውቋል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዘጋቢያችን እንደገለጹት፥ መመሪያው በማህበር የተደራጁ የንግድ ድርጅቶችን፣ የሸማች የህብረት ስራ ማህበራትን፣ በጥቃቅን ስራዎች የተደራጁ ማህበራትን፣ የገበሬዎች ማህበራትን፣ እድሮችን፣ ሌሎች በእርሻ ስራ የተሰማሩ አክሲዮኖችን እና የመሳሰሉትን ያካትታል። እንደ ምንጮቹ ገለፃ፥ ይህ በቅርቡ አገር አቀፍ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው መመሪያ ጣምራ አላማዎችን ከበስተጀርባው የያዘ ነው።
ወያኔ የአምስት አመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተብዬ ያወጣው በባዶ ካዝና ነው የሚሉት ምንጮች፤ አገዛዙ በአድሎ የሚሰበስበውን የግብር፣ የቅጣት እና የቀረጥ መጠን ለማሳደግ ካወጣው እቅድ በተጨማሪ ሌላ ገንዘብ ማግኛ መንገዶችን መወጠኑ ግድ ይለዋል ብለዋል። በተጨማሪም፥ ዜጎች በማንኛውም ሁኔታ ሲደራጁ የተቃዋሚ ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት ያለበት አገዛዝ ማህበራት ገንዘባቸውን በመንግስት ባንክ እንዲያስቀምጡ በማስገደድ እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር እንዲችል ነው በማለት አስረድተዋል።