ዳዊትና ጎልያድ፣ ብርቱካንና መለስ
አትክልት አሰፋ – ከቫንኩቨር(ካናዳ)
“አይ.. ኢትዮጵያ ሀገሬ…” አለ አንድ የቅርብ ወዳጄ። በዚያ በቅንጅት ዘመን እዚህ ግባ የማይባሉ ግለሰቦች፤ የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ካርድ ሰጭና ነሽ ሆነውበት አንጀቱ አሮ። ታዲያ ጊዜ አልፎ ጊዜ ተተካና ዛሬ መጣ ከርሞ ይመጣና ዛሬም ድሮ ይሆናል። ክፋቱ ሰው ቆሞ ይቀራል እንጂ ጊዜውስ ይበራል የጎልያድና የዳዊት የብርቱካንና የመለስ ፍልሚያስ ከተጀመረ ሁለት አመት ሞላው አይደል?።
ይህ የያዝነው 2003 ዓ.ም እንደገባ በኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር ማለቴ ነው የማህበራዊ ህይወት መድረክ መሆኑ በሚነገርለትና በአለም ዙሪያ 5መቶ ሚሊየን በላይ አባላት እንዳለው በሚታወቀው ፌስ ቡክ ( facebook) ላይ አንዲት በአራት አንቀጽ በምትገመት የተጠናቀቀች፤ ያዘለችው ቁም ነገር ሐልቆ መሳፍርት የሆነች መልእክት ጽዮን ግርማ በተባለች ጸሀፊ ጓደኛየ ተሰራጭታ ነበር። የብርቱካንንና የቤተሰቦቿን ስቃይ የሚያሳይ ጥንጥ ጽሁፍ።
አዎ ብረቱካን ስቃይ ውስጥ ነበረች፣ ምጥ ውስጥ ነበረች፣ እሷ ብቻ ሳትሆን እኛም ተጨንቀን ነበር በውጭም በውስጥም ያለን ኢትዮጵያዊያን፤ እንዲሁም አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን ሁሉ አሳስቧል፤መግለጫ በመግለጫ እንዲሆኑ አድርጓል፤ የብርቱካን ቤተሰቦች ስቃይ ግን ብርቱ ነበር። ከሁሉ የከፋ።
ጽሁፉ በሀገራችን የመጀመሪያ እንስት የፖለቲካ ድርጅት መሪና በአጭር ጊዜ የዳኝነት ስራዋ እውነተኛ ፈራጅ መሆኗን ያስመሰከረችውን ብርቱካን ሚደቅሳን ሁናቴ ያትታል። እንዲህ በማለት ነው ሲጀምር…
ቡርቴ ከታሰረች ጊዜ ጀምሮ ዕድል ቀንቶኝ አያት ይሆናል እያልኩ አለፍ አለፍ እያልኩ ቃሊቲ አመራለሁ። እንዳልኩትም እድል ቀንቶኝ አንዲት ቀን ለ30 ደቂቃ አየኋት! አናገርኳት! አጅሪት ከጥንካሬዋ እና ከሞራሏ ፍንክች አላለችም…..ያቺን ቀን ተደሰትኩባት፤ ከዛ በኋላ ወደ ቃሊቲ ግቢ ….ወደ ቡርቴ የመግባት መብትም ኾነ ዕድል አላገኘሁም….ግን በሩ ላይ ደርሼ እመለሳለሁ። ይላል የዚያች አጭር ጽሁፍ መግቢያ እናም ከትግራይ ክልል እስከ ሐረር ጥግ፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ አውራ ጋምቤላ እስከ ሀቀኞቹ ሀገር አፋር ድረስ እውነትን ፍለጋ የተንከራተተችው ጋዜጠኛ ጽዮን ለእውነትና በእውነት ብላ የታሰረችውን የቃሏ ምርኮኛ ወጣት ፖለቲከኛ ብርቱካንን ለመጠየቅ እያሰለሰች መገኛዋ ቃሊቲ እስር ቤት እንደነበር ስትገልጽ። ትቀጥላለች…
እናቷ ወ/ሮ አልማዝ….ልጇ ሀሌ…..እህቷ እሙሻ… ስንቃቸውን ሸክፈው ይገባሉ ከ40 ደቂቃ በኋላ ዘንቢላቸውን አንጠልጥለው ይወጣሉ፡፡የቅዳሜና እሁድ የተለመደ ተግባራቸው ይህ ነው… ከፈረንሳይ ቃሊቲ… ከቃሊቲ ፈረንሳይ። ይላል እናት የልጅ ልጃቸውን ይዘው ልጃቸው ወደታጎረችበት ቃሊቲ የሚያደርጉትን የዘወትር ተግባር ስትገልጽ።
እንደተለመደው ዛሬም እድል ቢቀናኝ ብየ ወደቃሊቲ አመራሁ፤ ሳይቀናኝ ቀረሁ። ራቅ ብየ ወ/ሮ አልማዝን አየኋቸው፤ በአንድ እጃቸው እንደ ከዘራ የሚያገለግላቸውን ጥላ ይዘዋል፤ በአንድ እጃቸው ደግሞ ስንቅ። ሃሌ የአክስቷን ቀሚስ ይዛ ትከተላለች… መኪና የሚበዛበትን መንገድ ቀስ እያሉ ተያይዘው ተሻገሩ፤ የበሩን ፍተሻ አልፈው ወደ ውስጥ ዘለቁ …። በማለት ትቀጥላለች በጽዮን የተጻፈችው አጭር ጽሁፍ። ጸሀፊዋ ይህችን አጭር ጽሁፍ ስትተይብ እያሰበች፣ እያሰላሰለች ወይንም ደግሞ ቃላቶችን ኑልኝ ወረቀት ላይ ላስፍራችሁ በማለት እየተማጸነች እንዳልሆነ በግልጽ ያስታውቃል። ያለምንም ጥርጥር እንደወረዱ እንደጅረት እየፈሰሱ በውስጧ ያለውንና ያየችውን ለእውነት ስትል ምስክርነቷን እንደሰጠች ያስታውቃል። ምስክርነቷም ይቀጥላል፣ እንዲህ ሲል…
… ከቆይታ በኋላ እንደተለመደው ጉዟቸውን ወደ ፈረንሳይ ጀመሩ… ምናልባት “ልጄ ለአዲስ ዓመት ትፈታለች” ብለው የጠበቁት መስከረም ያለ አዲስ ነገር ሁለተኛ ቀን ስላስቆጠረች ተስፋ ቆርጠው እንደሆን አላውቅም፤ ተዳክመው ታዩኝ… የማደርገው ነገር ባይኖርም ለቡርቴ እናትና ልጅ ልክ እንደዛሬው አዝኘ እና ልቤ ተሰብሮ አያውቅም ትላለች በአጭር የተቋጨችው ጽሁፍ። በወርሃ መስከረም መጀመሪያ በቃሊቲ በር ላይ የብርቱካንን ቤተሰብ ኑሮ ያስተዋለችው የአይን ምስክር። ጽሁፋን ስትደመድም በተስፋ ነበር። አዎ ተስፋ። በኢትዮጵያ ላይ የፈለጋቸውን ለማድረግ ሲያሰኛቸው ለማሰር ሲፈልጉም ለመግደል ወይ እግዚአብሄር እንዲያም ካለ ህዝብ ከፈቀደላቸው ከአሳሪና ፈችዎች እጅ እንድትላቀቅ ሰማይ ላይ ላለ እግዜርም ተስፋዋን ታደርሳለች።
… ከእስር እንድትፈታ ልቤ አጥብቆ ተመኘላቸው… የጀግናዋን እናት ከልጃቸው… የጀግናዋን ልጅ ከእናቷ በቅርቡ በጣም በቅርቡ ያገናኛቸው ዘንድ እንጸልይላቸው። ከዚህ ውጭ ሌላ ምን ኃይል ይኖረናል….። በማለት ነው አጭሯ ነገር ግን የያዘችው መልእክት ድንቅ የሆነችው መጣጥፍ የተጠናቀቀችው።
አንድ ነገር እረዳለሁ ጸሀፊዋ የምንም አይደለችም የዚያ ወይም የዚህ የቅንጅት አለያም የኢህአዴግ፤ የአንድነት ወይ የህወሀት እንዲያም ካለ የመድረክም የግንቦት ሰባትም አይደለችም። የእውነት እንጅ። ያየችውን ወላጅ ለታሰረች ልጃቸው ሊመኙ የሚችሉትን ተስፋ አየችላቸው። ተስፋዋ የሁላችን ነበር እናም ተፈጸመ።
የብርቱካን ፈተና ብዙ ነበር። እጅግ ብዙ። ሀገር፣ እናት ፣ ልጅ ፣ ህዝብ፣ እውነት፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ፣ እስር እንግልት፣ ሞት፣ ህይወት የነኝህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ነበረባቸው ከፊት ለፊቷ ቆሞ ሊገጥማትና ሊፋለማት ደግሞ ጎሊያድ ቆሟል። መለስ።
መለስና ጎልያድ አንድ ናቸው። ጎልያድ ብዙ እጅግ ብዙ አጫፋሪዎች ነበሩት። ብዙ የሚያወሩለት። ኃይለኛነቱንና ጉብዝናውን የሚተርኩለት፤ ጎልያድ ደንታ አልነበረውም ጦሩ በሱ መንግስቱ በሱ፤ ሁሉን ማድረግ የሚችል ጉልበተኛ። ጎልያድ እንደመለስ ነው። ሲያሻው የሚያስር ሲፈልገው በ10 ዓመት ህጻን ልጅ ግምባር ውስጥ ጥይት እንዲተኮስ የሚያዝ። እንዲያም ሲል ይቅርታ በሉኝ ብሎ ንጹሀንን የሚያንገላታ በዛ ስቃይም ልቡ በሀሴት የሚደልቅ።
መለስ ጎልያድ ነው። ልቡ ያበጠ ያሻውን የሚያደርግ። ግን ግን አንድ ቀን ጓዴ እንደሚላት ብርቱ ካህን መጣችበት የ34 ዓመት ወጣት ሴት፣ አለሁ አለች ቃሏን ጥይት አድርጋ፣ በራሱ ቃል የማይጸናውን ጎልያድ መለስን ልትፋለም። በመረጠው መንገድ፣ በከፈተው ቀዳዳ ልትተናነቀው ተነሳች፤ ከጎኗም ሰው አስከተለች፣ ለነጻነት ፍልሚያ መለስ-ጎልያድን ገጠመች፤ በራሱ መንገገድ በራሱ ሜዳ ግን ግን መች ወንድ ሆነና ወንድ አላገኘችም፣ ወንድ አልገጠማትም ጎልያድ እንጂ፤ በአጫፋሪዎች የተከበበ፣ መንግስቱ ሁሉ በሱና ለእርሱ የሆነ።
እናም መለስ-ጎልያድ ያለውን ኃይል ሁሉ ተጠቀመ፤ ብርቱካን ግን ከቃል ውጭ ቃል የላትም፤ ማየት ነበር ስራዋ የዚያን አረመኔ ድርጊት ለማንም እንደማይራራ ታውቃለች፤ ለማንም። መለስ ለሚስቱም የሚመለስ አይደለም ወይ ለልጆቹ። አንዳንዴ ሳስበው ለሚስቱ ለማውረስና የመጀመሪያ ሴት ጠ/ሚኒስትርና የፖለቲካ መሪ የማድረግ ህልሙን ብርቱካን ቀጭታበት ይሆን ይህችን ሴት ብቻዋን የቸነከራት እላለሁ። እውነት እውነት እላለሁ ይህ ሰው ለማንም አይመለስም።
ዳዊት ምንም ብረት የሌለው እንደብርቴ የመንፈስ እንጂ የፈረጠመ ክንድ የሌለው ነበር፤ ግን ፈሪ አልነበረም የሚያደርገውን የሚያውቅ ልበ ሙሉ እንጂ። ለዚያም ነው ጎልያድን፣ ያንን በመጥፎነቱ የሚታወቅ ግዙፍ አካል የገጠመው። ልክ እንደ ብርቴ እንደ ብርቱካን።
ብርቱካን መለስ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ ሁለት አመት ስትታሰር የህዝቧን ስቃይ ነበር የተሸከመችው ልክ እንደ ዳዊት ሁሉ እሷም ያላት ምርጫ ማሸነፍ ነው። ዳዊት ወንጭፉ ነበር ያለው። ብቸኛ አማራጩ፤ የብቱካን ግን ለየት ይላል፤ ያላት ወንጭፍ ለ21 ወራት ባሳለፈችው የጸጥታ ጊዜ የጎነጎነችው ወንጭፍ ፍቅር ነበር፤ በፍቅር ጎልያድን መጣል። አምጣው እንዲሆን የምትፈልጋቸውን ደብብዳቤዎች አምጣቸው እናም ልፈርምልህ። ብላ ከንፈሯን ጣል አድርጋ ያሾፈችበት ይመስለኛል። እናም ልፈርምልህ የምትፈልገውን ረቂቅ ላክልኝ ነበር መልሷ እናም ልፍስፍሱ መለስ ወደኋላ አላለም ላከላት እንዲያውም የሚገርመው ኖኖኖኖ የሚቀር አለ። አለ መለስ ደብዳቤው ላይ የሚቀር የሚጨመር አለ። የውጭ መንግስታት ያስፈቱኛል ብየ …በይበት። አለ። ሌላም ቀርቷል ይህንንም አክይበት በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ይጮሁልኛል ብየ በይበት፤ የቀረሽ ነገር አለ…. ጨምሪበት። ሌላም… ሌላውም… ታከለ፤ ተደረደረ። እውነት ይሄንን የሚለውን በመድገም ከሚያደነቁሩ ካድሬዎቹ ውጭ የሚያምን ይኖር ይሆን?።
እንደኔ እንደኔ በዚህ በአለንበት ወቅት ቢሆንና በራሳቸው ዜጎች ጭቆና ውስጥ ቢወድቁ ጋንዲም፣ ማንዴላም፣ ማርቲን ሉተርም ቢሆኑ ከዚህ ውጭ የሚያደርጉት አማራጭ ነገር ያለ አይመስለኝም። የሚኖረው አማራጭ ይህ ብቻ መሰለኝ። እንደዚያ ዘመኑ አንዳንድ ሀገራት ይፈቱ ከማለት ውጭ ቆራጥ እርምጃ አይወስዱም። ይጮሀሉ እንጂ አይናከሱም። ፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ ሰብአዊ መብት አልተከበረም ይላሉ። ይናገራሉ እንጂ መንግስታት ማእቀብ አያደርጉም። ቆራጥ አይሆኑም እንዲያው ለአሳሪው አገዛዝ ብድር በመስጠት ያበጠውን ልብ ያሳብጡለታል። ለዚያም ነው እነማንዴላ ዛሬ ላይ ሆነው በቡርቴ ተሳሳትኩ መሰል በብርቴ ቦታ ቢሆኑ የእሷን እርምጃ ይወስዱ የነበረው።
መቸም ፍቅር ትበልጣለች ነው ያለው መጽሀፉ? የብርቴ መልስ አንድ ነበር የሚያስደስትህን አምጣው እፈርማለሁ እናም ነጻ እሆናለሁ። የዳዊት ወንጭፍ በብርቱካን ፍቅር ተተካ የጎልያድ ሞት በመለስ የቁም ሞት ተለወጠ። ‘ኢትዮጵያ ሀገሬ…’ አለ የዋሁ ወዳጄ ሴት ወንድ ወንድ ሴት ሆነብሽ።
ቸር ለሁላችን