በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን እና ኮሚኒውኬሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የሚሰሩ ሰራተኞች የተቋሙን ዘረኛነት አማረሩ
በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሚውኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ አንዳንድ ሰራተኞች በተቋሙ ውስጥ አለ ስለሚሉት ዘረኛነት ማማረራቸውን የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሰው ዘገባ አስታውቋል።
ለአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ስሞታቸውን ያሰሙት ግለሰቦች፥ የወያኔ ሹም በሆነው ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከሚመራው ተቋም ሰራተኞች ውስጥ ከ90% በመቶ በላይ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች ናቸው ; ይህም ሊሆን የቻለው ተቋሙ በዘር አድሎ ላይ ተመስርቶ ሰራተኞችን ስለሚቀጥር ነው ሲሉ ገልጸዋል። የዝግጅት ክፍላችን የዚህን ቁጥር እውነተኛነት ከሌሎች ምንጮች ለማጣራት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው ያልተሳካ ይሁን እንጂ በወያኔ አገዛዝ ስር ተቋማዊ ዘረኛነት በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የመስሪያ ቤቱ ህጋዊ የስራ ቋንቋ አማርኛ ቢሆንም፤ ከትግራይ ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ መሆን የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ የሚወራው ትግርኛ እንደሆነና አንዳንድ ጊዜ መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ሳይሆን መቀሌ ያለ እንደሚመስላቸው ሰራተኞቹ ተናግረዋል። ይህም ከስራቸው የመገለልን እና የእንግዳነትን ስሜት እንደፈጠረባቸው እና፤ የህዝብ ንብረት በሆነው ተቋም ላይ እንደ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸው መደረጋቸውን በስሞታቸው አክለዋል።
ሰራተኞቹ በመጨመርም፥ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አቻዎቻቸው በነፃነት መንቀሳቀስ እና መስራት ሲችሉ፤ እነሱ ግን እንደማይታመኑ እና በስራቸው ላይም ሆነ በእረፍት ሰዓት ሻይ ለመጠጣት ሲወጡ ክትትል እንደሚደረግባቸው አስረድተዋል።