የወያኔ ተለጣፊ ፓርቲ የሆነው ኦህዴድ ለሶስት ተከፈለ፤ አባ ዱላ ገመዳ ከሊቀመንበርነቱ ተነሳ

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ወይም ኦህዴድ) በመባል የሚታወቀው የወያኔ ተለጣፊ ፓርቲ ለሶስት መከፈሉና በኩማ ደመቅሳ የሚመራው ቡድን አሸናፊ ሆኖ መውጣቱ ታወቀ።

ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለግንቦት 7 ድምጽ ካደረሱት መረጃ እንደተረዳነው፥ በፓርቲው ውስጥ በኩማ ደመቅሳ እና በአባ ዱላ ገመዳ የሚመሩ ትላልቅ ቡድኖች እና በጁነዲን ሳዶ የሚመራ አነስ ያለ ጎራ ተፈጥረው ለተወሰነ ጊዜ ሲሻኮቱ ቆይተዋል። በጎራዎቹ መካከል የነበረው ልዩነት መሰረታዊ ባህሪ የሌለው እና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባ፤ በተለይ በአባ ዱላ እና በኩማ ደመቅሳ የሚመሩት ቡድኖች የመለስ ዜናዊን ድጋፍ ለማግኘት ሲሯሯጡ እንደሰነበቱ እና በስተመጨረሻም የኩማ ደመቅሳ ቡድን የዘረኛውን አምባገነን ድጋፍ እንዳገኘ ለማወቅ ተችሏል።

ፓርቲው ሰሞኑን በአዳማ ባደረገው ስድሰተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይም ይኸው የኩማ ደመቅሳ ቡድን በአሸናፊነት በመውጣት ሊቀመንበሩን አባ ዱላን በመሻር አለማየሁ አቶምሳን ሹሟል። አባ ዱላ ገመዳ በአሁኑ ሰዓት የኦሮምያ ክልል ፕሬዚደንትም ሲሆን፤ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠው ሙክታር ከድር ያንንም ቦታ ሊረከበው እንደሚችል ያለውን ግምት ዘገባው ጠቁሟል።

የደረሰን ዘገባ ጨምሮ እንደሚገልጸው፥ አባ ዱላ እና የሚመራው ቡድን በተለይ ከመሬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ባካበቱት ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ። እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ዘገባ መለስ ዜናዊ የአባ ዱላን ቡድን የሚቃወም መስሎ ለመታየት እንደሚሞክርና በኦህዲድ ውስጥ የተፈጠረው የርስ በርስ ርኩቻ ውስጥ ለውስጥ እንዲባባስ ጥረት እንደሚያደርግ ይህም ኦህዲዶች አንድ የመሆን አዚማሚያ ካሳዩ ከወያኔ ጋር ያላቸው ኢፍትሃዊ የጥቅም ግንኙነት አይናቸውን እንዲገልጡ ያደርጋቸውና በአገዛዙ ላይ የማኩረፍ ዱለታ ውስጥ ሊከታቸው ይችላል ከሚል ስጋት እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ዘረኛው መለስ ዜናው በሚቀጥለው የሚንስትሮች ሹመት አባ ዱላ ገመዳን በአዲሱ ለገሰ ምትክ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት አጭቶታል የሚል ተባራሪ ወሬ በቤተመንግሥት ዙሪያ እየተነዛ መሆኑን እንደማስረጃነት ያቀርባሉ። በዚሁ የኦህዴድ ስብሰባ ላይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሃላፊ ጁነዲን ሳዶ እና የቀድሞ የፓርላማ የወያኔ አገዛዝ ተጠሪ ሽፈራው ጃርሶ በማእከላዊ ኮሚቴው የነበራቸውን መቀመጫዎች አጥተዋል።

ዘገባውን ያደረሱን ውስጥ አዋቂዎች፥ የኩማ ደመቅሳ ማሸነፍ እንደተለመደው የመለስ ዜናዊን እድሜ ከማራዘም ውጪ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር የሚያበረክተው እንደሌለ፤ በድርጅቱ ውስጥ እንደፈለገው የሚወስነው እና የድርጅቱ ራስ እና ጉልበት መለስ ዜናዊ እንደሆነ የኦሮሞ ህዝብ ሊረሳ አይገባም ብለዋል።