የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው አሰግድ ተፈራ አገር ጥሎ ወጥቶ በስደት እንደሚገኝ ታወቀ
ለረዥም አመታት የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ያገለገለው ጋዜጠኛ አሰግድ ተፈራ በተደጋጋሚ ሲደርስበት በነበረው ማስፈራሪያ፣ ድብደባና የግድያ ሙከራ ምክንያት መሰደዱን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ ዘገባ አሳይቷል።
አሰግድ ተፈራ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ በነበረባቸው አመታት በርካታ የሙስና ወንጀሎችን የሚያጋልጡ ዘገባዎችን በማጠናቀር የሚታወቅ ሲሆን፤ ከበርካታ ወራት በፊት የወያኔ ደጋፊ ከሆነው ሼክ አላሙዲን ኩባንያ ጋር የተያያዙ ተከታታይ ሪፖርቶችን ማቅረቡ ይታወሳል። ጋዜጠኛው ከደረሱበት ተደጋጋሚ ዛቻዎች እና ድብደባ በተጨማሪ ከነቤተሰቡ በሚኖርበት ቤት ላይ ቦምብ ሊጣል ሲል በጎረቤቶቹ እርዳታ መትረፉን ተናግሯል።
በመጨረሻም የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆነው ብርሃኑ አዴሎ ጋዜጠኛው ሪፖርተርን ለቆ የሰነድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንዲሰራ እንዳስገደደው አስረድቷል። ሰነድ ጋዜጣ የብርሃኑ አዴሎ ንብረት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። ለአራት ወራት ያህል ግዳጁን ተቀብሎ ሰነድ ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት ማገልገሉን የገለጸው አሰግድ፤ አራስ ልጁን ጥሎ ከባለቤቱ ጋር መሰደዱን ተናግሯል።