ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔው አገዛዝ የርቀት ትምህርት በኢትዮጲያ እንዳይሰጥ ከለከለ
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የርቀት ትምህርት እንዳይሰጥ የከለከለ ሲሆን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ህግና መምህራን ስልጠና ትምህርት እንዳይሰጡ አግዷቸዋል።
ይሄው ባሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች አነጋጋሪ የሆነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚመለከተው መመሪያ ርምጃው የተወሰደው በዘፈቀደ መሆኑን ይህም የተማሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ዜጎች ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ምክትል ዋሾ የሆነው በረከት ስምዖንን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ባለሥልጣናት ከኢንተርናሽናል ሊደርሽፕ ኢንስቲትዩት በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ ኤንድ ቼንጅ በድኅረ ምረቃ በቅርቡ እንደሚመረቁ ለአገዛዙ ቅርበት ያለው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት መዘገቡ ይታወቃል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለዘጋቢያችን በሰጡት አስተያየት የወያኔው አገዛዝ ባለስልጣናት የራሳቸውን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎች በርቀት ትምህርት በገንዘባቸውና በስልጣናቸው በጃቸው ካደረጉ በኋላ ይህ አይነት ውሳኔ መተላለፉ ወያኔ ለዜጎች ምንም ቅንጣት ያህል ደንታ የሌለው መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ አሜሪካ ቪ ኦ ኤ ሬዲዮ ዘገባ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዚደንት ‘’በግሉ ተቋማት የጥራት ችግር ያለባቸው እንዳሉ አይካድም፤ የሚያሳዝነው የዘርፍ ችግር ተደርጎ መወሰዱ ነው” ማለታቸውንም ታውቋል።