‘’የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ’’
“በአይኑ ምሰሶ ይዞ ከሌላው አይን ጉድፍ ላውጣ ይላል”፤ “አመድ በዱቄት ይስቃል”…እና የመሳሰሉት፤ አባቶቻችን ከሃይማኖት እና ከልምድ ወስደው የባህል እና ቋንቋችን አካል ያደረጓቸው አባባሎች ናቸው። ሃፍረተ-ቢስነትን እና ግብዝነትን ይገስፃሉ። በሌሎች ከመፍረዳችን በፊት እራሳችንን አጥርተን እንድንመለከት ይጋብዙናል።
ዛሬ እነዚህን አባባሎች እንድናስታውስ ያደረገን፤ የወያኔ አገዛዝ በትምህርት ጥራት ስም የተልእኮ ትምህርትን አገደ የሚለው ዜና ነው። የአሜሪካ ድምጽ በጉዳዩ ላይ እንደዘገበው፥ በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሙሉ የተልእኮ ትምህርት መስጠታቸውን እንዲያቆሙ አዟል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አበራ አባተ አበበ፥ እገዳው የተጣለው የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ ሲባል ነው እንዳለና ብዙ የግል ትምህርት ቤቶች ትርፍ ማግኘት እንጂ ጥራት ያለው ትምህርት የመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው መግለጹን የአሜሪካ ድምጽ በዘገባው አክሏል። ይህን ምክንያት እውነት ነው ብለን ብንቀበለው እንኳ፣ “ታዲያ የህዝብ ትምህርት ቤቶችስ ለምን ታገዱ?” የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ከዚህም በተጨማሪ፥ የግል ትምህርት ቤቶች የህግ እና የአስተማሪነት ዲግሪ ፕሮግራሞች እንዳያቀርቡ የታገዱበት ምክንያት አልተገለጸም። ይሁን እንጂ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ይሄ አይደለም።
በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ኢትዮጵያ፥ የትምህርት ጥራት ደረጃ፣ መሬት ነክቷል ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ ቀልደኞች እንደሚሉት፣ መሬት ከወደቀም በኋላ ወደታች መቆፈር ጀምሯል። ይህ አሳዛኝ ሃቅ ብዙ የተወራለት ነው። የዛሬው ሃተታችንም ይህንን ሃቅ የሚከራከር አይደለም።
የወያኔ አገዛዝ ለትምህርት ጥራት ስል የተልእኮ ትምህርትን አገድኩኝ ማለቱ ግን በብዙ ምክንያት አስቂኝ ነው። አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ለከፈላቸው ሁሉ ዝም ብለው ዲግሪ ይሰጣሉ ብሎ ተቆጪ ሆኖ መቅረቡም ፈገግ ያሰኛል። እነሆ በአይኑ ምሰሶ ይዞ ከሌላው አይን ጉድፍ ካላወጣሁ የሚለው ግብዝ ወይም አይን አውጣ ሰው ምሳሌ!
የዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት ያውም የህዝብ ገንዘብ እያፈሰሱ፣ ለአንድ ዲግሪ እስከ አስር ሺህ የአሜሪካ ዶላር እየከፈሉ ከውጭ አገራት የተልእኮ ትምህርት ተቋማት የምስክር ወረቀቶች መሰብሰባቸው ይታወቃል። ያንን ሁሉ የህዝብ ገንዘብ አፍስሰው ቢማሩ ደግሞ አንድ ነገር ነበር። ይልቁንስ በስማቸው ፈተና እየወሰዱ እና የቤት ስራዎቻቸውን እየሰሩ የማለፊያ ውጤት የሚያስገኙላቸውን ሰዎች በጎን ይቀጥራሉ። የዚህ የወንበዴዎች ቡድን ቁንጮዎች ምሁራንን ከአገሪቱ በማሳደድ የአገሪቱን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወና አድርገው የትምህርትን ጥራት አፈር ማስበላታቸው ሳያንስ፤ በግላቸውም እንደዚህ ሲሳለቁ ቆይተዋል።
የወያኔ ባለስልጣናት የትምህርት ደረጃን እና ጥራትን በሚመለከት ያልሰበሩትና ያልተረማመዱበት ህግ የለም። አንድ ሰው የመጀመሪያ ዲግሪ ሳይዝ ሁለተኛ ዲግሪ ሊኖረው አይችልም የሚለው የምህርት ሚኒስቴር ህግ፤ ባለፉት ሃያ አመታት የወያኔ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች መረማመጃ ሆኖ ቆይቷል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንኳ ያልጨረሱ ካድሬዎች ከውጭ አገር በህዝብ ገንዘብ የተገዛ የማስትሬት ዲግሪ ምስክር ወረቀት እየያዙ ወደየመንግስት መስሪያ ቤቱ በመግባት ያለብቃታቸው ስልጣን እና የደሞዝ ጭማሬ ሲንበሸበሹ ቆይተዋል። አሁን እነዚህ ዱርዬዎች ናቸው ለትምህርት ጥራት ዘብ ጠባቂ የሆኑት?!
መልስ ተሰጥቷቸው ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ የተቀመጡ፤ በውሸት ያገኙትን ከፍተኛ ውጤት አንጠልጥለው “ድንጋይ ፋብሪካ” የሚል ቅጽያ ስም ከወጣለት የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የገቡ እና እዛም ሄደው ተምረው ፈተና ማለፍ ስላልቻሉ መስፈርቱ ሁሉ ዝቅ ተደርጎላቸው በገፍ የተመረቁ። ድንቄም የምህርት ጥራት ጉድለት ተቆርቋሪዎች!
ለመሆኑ በተልእኮ ትምህርት ላይ የተደረገው እገዳ የውጭ አገሩንም ይጨምር ይሆን? ለነገሩ ቢጨምር ባይጨምር እነሱን ምን ገዷቸው። ማስትሬት ዲግሪ እንደሆነ እስካፍንጫ ተሰብስቧል።
እንግዲህ ውንብድና እና ዘረፋን የማንነቱ ማእከል ካደረገ ቡድን እንዲህ ያለ ሃፍረተ-ቢስነት እና ግብዝነት ቢመጣ አይገርምም። እኛም ስለጉዳዩ የምናወራው አገራችንን በጉልበት ተቆጣጥሮ ስላለው ስርአት ማንነት ለማስታወስ ብቻ ነው። ይህ፥ እየሰረቀ አትስረቁ፤ ህግ እየሰበረ ህግ አክብሩ፤ እየገደለ አትግደሉ፤ አገር እያፈረሰ ሌሎችን ጸረ-ሃገር፤ ህዝብ እየጨቆነና እያስጨነቀ ሌላውን ጸረ-ሰላም የሚል ቀልደኛ የሆነ የቦዘኔዎች ስብስብ ነው። ይህንን የወንበዴ ቡድን ደግሞ ዛሬ ላይ ቆመው እንደ መንግስት የሚቆጥሩ ካሉ ወይ አውቀው የተኙ አልያም የየዋሆች የዋህ ናቸው። እንደዛ አይነቶቹን ደግሞ ሊያድን የሚችለው የፈጠራቸው ብቻ ነውና የኛ መልክት ለነቁቱ ነው።
የነቁትን ተነሱ እንላለን፤ አገራችን መሳለቂያ እና የቦዘኔዎች መጨፈሪያ መሆኗ ያብቃ። ተባብረን እንነሳና በእውነት እና በውሸት መካከል ያለውን መስመር እናድምቅ!