የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ የመረጃ ምንጮቹን እንዲያሳውቅ በወያኔ አገዛዝ መታዘዙን ገለጸ
በኢትዮጵያ ውስጥ ከቀሩት እና በከፍተኛ አፈና ስር በመጠኑም ቢሆን ከሚንቀሳቀሱት ጥቂት ገለልተኛ የግል ጋዜጣዎች ውስጥ አንዱ የሆነው አውራምባ ታይምስ በወያኔ አገዛዝ ህገ-ወጥ ትእዛዝ እንደተሰጠው ሐሙስ እለት በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፍ አስታውቋል።
በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታ ተስፋው ጋዜጣው ለዜና ዘገባ የሚጠቀምባቸውን የመረጃ ምንጮች እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቅ ትእዛዝ ሰጥቷል።
“በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሠረት አንድ ጋዜጠኛ ለፍርድ ቤቶች ሳይቀር የመረጃ ምንጭ የማሳወቅ ግዴታ እንደሌለበት በግልጽ የተደነገገ ቢሆንም ብሮድካስት ባለስልጣን በ‹ሬጉላቶሪ› ሽፋን ሕገ መንግስቱን የሚጥስ ጥያቄ መጠየቁ የጋዜጣው ባልደረቦችን አስገርሟል፡፡” ሲል አውራምባ ታይምስ በድረ-ገጹ ባሰፈረው ዘገባ ገልጿል።
“ከዚህ በተጨማሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ሀላፊነት ውጪ ጋዜጣው ከሽያጭና ከማስታወቂያ የሚያገኘውን የፋይናንስ ሪፖርት እንዲያሳውቅ የጠየቀ ሲሆን ይህን የመጠየቅ ኃላፊነት የተጣለበት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መሆኑ እየታወቀ ብሮድካሰት ባለስልጣን ይህንን መጠየቁ ብዙዎችን አስገርሟል፤” ብሏል።