ቢሳካለት ለአቅመ አዳም ከደረሰው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ስደትን እንደሚመርጥ ጥናቶች አረጋገጡ
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንድ መቶ አርባ ስምንት ሃገራት ላይ በተደረገ ጥናት አገርን ለቆ በስደት የመኖር እድሉን ቢያገኝ 46 በመቶ የሚሆነው ለአቅመ አዳም የደረሰ ኢትዮጵያዊ ሃገሩን እየጣለ ወደስደት ዓለም መግባትን እንደሚመርጥ በቅርብ ቀን የወጣ ጽሁፍ አረጋገጠ። ይህን ጥናት ያካሄደው የሰው ልጆችን ባህሪ በማጥናት የ75 ዓመታት ልምድ ያለው ጋሉፕ በመባል የሚታወቀው ድርጂት ነው።
ይህ ድርጂት ባወጣው ጽሁፍ እንደተገለጸውና በቅርብ ቀን የተካሄደውም ጥናት እንደሚያረጋግጠው በጥናቱ ከተካተቱት 148 ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ከሚገኙት ጥቂት ሃገራት ውስጥ እንደምትካተት ገልጿል። ዜጎቻቸው ስደትን በመምረጣቸው ከኢትዮጵያ ተርታ ከተሰለፉት ሃገራት ውስጥ ሃይቲ፤ ዚምባብዌ፤ ናይጀሪያና መንግስት የለሿ ሶማሊያ ይገኙበታል.። ባንጻሩ ዜጎቻቸው ስደትን የማይፈልጉ ናቸው በመባል የቀዳሚነቱን ስፍራ ከያዙ ሃገራት ውስጥ ሲንጋፖር፤ ንውዚላንድ፤ ሳውዲ አረቢያ፤ ካናዳ፣ ስዊትዘርላንድና ኩየት እንደሚገኙበትም ታውቋል።ከዚሁ ጋር በማያያዝ የጥናት ጽሁፉ እንደገለጸው ለነኝህ ስደተኞች የማረፊያ ቦታነቱን ቅድሚያ የምትወስደው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ መሆኗን ይኸው መግለጫ አክሎ አስታውቋል።
ይህን መግለጫ አስመልክቶ በስዊድን በስደተኝነት የሚኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ በሰጡን አስተያየት የራሱ የወያኔ ባለስልጣናት ዘመድ አዝማድ ስልጣንን መከታ በማድረግ ቪዛ እየወጣላቸውና በሃሰት የስደት ወረቀት ማግኘት የሚችሉበት የሃሰት ማስረጃ እየተፈበረከላቸው በሁሉም የአውሮፓና የአሜሪካ ሃገራት የጥገኝነት መጠያቂያ መስሪያ ቤቶችን ማጣበብ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። በዚህም የተነሳ በጥናቱ ላይ የተመለከተው 46 % እውነተኛውን አሃዝ ከሚገልጽ በታች ቢሆን እንጂ የሚያጠራጥር አይሆንም ብለዋል።
የዳብል ዲጂት እድገት እያሳየሁ ነው እንደኔ ያለ መንግስት የለም የሚለው ወያኔ የሚገዛት ኢትዮጵያ በዜጎቿ ስደተኝነት ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያና የፖለቲካ ቀውስ አለባቸው ከሚባሉት የአፍሪካ ሃገራት በእጥፍ እንደሚበልጥ ይታወቃል።