አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ለጋዜጠኞች የሰጠው ቃለመጠይቅ የተለመደና ቅጥፈት የተሞላበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጠብመንጃ ካነሱና ከሌሎችም ያኮረፉ ድርጂቶችም ሆነ ግለሰቦች ጋር እደራደራለሁ ከማለት አንስቶ በመጪው አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በፍጹም በድህነት ስሟ አትጠራም በማለት ለጋዜጠኞች የሰጠውን ቃለመጠይቅ አስመልክቶ በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተለመደና ቅጥፈት የተሞላበት ንግግር ነው በማለትና በማጣጣል አስተያየታቸውን የሰጡት መሆኑን ዘጋቢያችን ከላከልን ዘገባ ለመረዳት ችለናል።

ዘጋቢያችን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ይህ የአሁኑ የመለስ ንግግር አዲስ ያልሆነና ስብእናውን የበለጠ በማጉላት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያላገጠ ያለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ ባለፈ መልኩ ግን የምእራቡን ዓለም ድጋፍ ለማግኘት ሲል የተጠቀመበት ማጭበርበሪያ ነው ብለዋል። ነዋሪዎቹ በተለይም መለስ በመጪው አምስት ዓመታት ውስጥ ሃገሪቱ ምንም የምግብ ርዳታ ከማትጠይቅበት ደረጃ ላይ አደርሳታለሁ፤ የምግብ ዋስትና ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል ብሎ መናገሩ ፍጹም የማያሳፍረውና ከ15 አመታት በፊት ተመሳሳይ ቃል መግባቱንና እንኳን እንደተናገረው ሊሆን ችግራችን ከነበረበት ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ መሸጋገሩን የዘነጋ ነው ብለውታል።

እነኚህ አስተያየት ሰጪዎች አክለውም መለስ ሃገሪቱን በምግብ ራሷን አስቺላለሁ በማለት በመገታቱ እናመሰግነዋለን፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍጆታ አትርፌ ለመላው ዓለም የምግብ እህል አቀርባለሁ ወይንም እሸጣለሁ ብሎ ቢናገርስ ይችል አልነበር በማለት የምጸት አስተያየት መስጠታቸውን ዘጋቢያችን በላከልን መልክት ገልጾልናል።