የአውራምባ ታይምስ ጽ/ቤት ባልታወቁ ግለሰቦች ጥቃት ተፈጸመበት፤ በጥቃቱ የጽ/ቤቱ የጥበቃ ሰራተኛ ክፉኛ የተጎዳ መሆኑ ተገለጸ

ነሃሴ 11 ቀን 2002 ዓ.ም ከሌሊቱ ስምንት ሰአት ላይ ሲሆን ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ወደ ጽ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ለመዝለቅ መሞከራቸውን በዚሁ እለትም ይህ ሙከራ ከመደረጉ ስድስት ሰአታት ቀደም ብሎ ግርግር ተፈጥሮ እንደነበርና ይህም ግርግር ሌሊት ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበረው የአይን እማኞችን በመጥቀስ ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ በላከልን ሪፖርት አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዚሁ እለት እነኚህ ማንነታቸው ያልታወቁት ግለሰቦች የተፈጠረውን ችግር በሰላም ለመፍታት ያደረገውን ጥረት ተከትሎ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ኤዲቶር የሆነውን ግዛው ለገሰን ማስፈራሪያና ወቀሳም እንደሰነዘሩበት በወቅቱ ችግሩ ሲከሰት ያዩ እማኞች እንደገለጹለት ዘጋቢያችን ገልጿል። በሌላም በኩል ከአውራምባ ታይምስ ጽ/ቤት ችግሩን አስመልክቶ ህጉ በሚያዝዘው መሰረት በወቅቱ ለሚመለከተው የፖሊስ ጽ/ቤት ሪፖርት የተደረገ ቢሆንም የተሰጠው ምላሽ አሳዛኝ እንደሆነበት የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲቶር መናገሩን ለጽ/ቤቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች መግለጻቸውም ታውቋል። ፖሊስ ሪፖርት ከተደረገለት ጊዜ እጂግ ዘግይቶ ወደ አውራምባ ታይምስ ጽ/ቤት መምጣቱን፤ ነገር ግን እንኳን የተፈጠረውን አጠቃላይ ችግር መፍትሄ መፈለግ ይቅርና የጥቃቱ ሰለባ የሆነውን የጽ/ቤቱ ዘበኛ ለማናገር ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ዘጋቢያችን ጨምሮ ገልጿል፡፡

የችግሩን ሂደት በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩና ስማቸው እንዳይገለጥ የጠየቁ የአይን እማኝ በተለይም ፖሊስ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት አለመተባበሩ እጂግ አሳፋሪና አሳሳቢ እንደሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውም የፖለቲካ ችግር እጂግ እየተወሳሰብ እንደመጣ ተናግረው ከዚህ የአውራምባ ጽ/ቤት ጥቃት በስተጀርባ አዛዥ ሃይል እንዳለ ምንም የማይጠራጠሩ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።