የኢትዮጵያው አስር በመቶ እድገትና ዘጠና በመቶ ድህነት

“የኦህዴድ ሰዎች በነጋ በጠባ ልማት ልማት እያሉ ይጨቀጭቁናል እኛ የተረፈን ልማታቸዉ ሳይሆን እርግጫቸዉ ነዉ፤ እንኳን የመኪና መንገድ ወደ ጨረቃ የሚወስድመንገድም ቢሰሩ እኩለነታችን እስካልተረጋገጠ ድረስ እኔ ለነሱ ድምፄን አልሰጥም” ስሙ የማይታወቅ ኢትዮጵያዊ ገበሬ

ይህ አባባል እዉቁ የብሉምበርግ ጋዜጠኛ ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ በአጋጣሚ አግኝቶ የጠየቀዉ የአንድ ገበሬ ብቸኛ ስሜት አይደለም። ወይም አባባሉ የወያኔ ጀሌዎች እንደሚያስወሩት ለስልጣን የቋመጡየጥቂት ግለሰቦች እምነትም አይደለም። አባባሉ የወያኔ ግፍና በደል ያንገፈገፋቸዉ ኢትዮጵያዉያን ሐይማኖት፤ዘርና ፖለቲካ ሳይከፋፍላቸዉ በጋራ የሚያሰሙት ህዝባዊ እሮሮ ነዉ።

ላለፉት 19 አመታት የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ መታዘብ ከሚችለዉ በላይ ዋሽተዉታል። ዘንድሮማ ዉሸታቸዉ ተዋሽቶ ተዋሽቶ ያለቀባቸዉ ይመስል የራሱን ህዝብ መቀለብ አቅቶት በምዕራባዉያን ድጎማ የሚንገዳገደዉን ኤኮኖሚ በእጥፍ ድርብ አደገ እያሉ መቀለድ ጀምረዋል። የሚገርመዉ እነሱ እድገትና ዲሞክራሲ እያሉ ይጩሁበት እንጂ ህዝቡማ የወያኔ ዘረኞች ለራሳቸዉና ለተወለዱበት አካባቢ ጥቅም ብቻ የቆሙ ጎጠኞች መሆናቸዉን ካወቀ ዉሎ አድሯል። ዘረኛዉ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ በከፍተኛ ፍጥነት አደገ የሚሉት ኤኮኖሚ ስግብግቦቹን የወያኔ ባለስልጣኖች የማይጠረቃ ሆድ ከመሙላት አልፎ የደሃዉን ኢትዮጵያዊ የምግብ ፍጆታ በአንዲት ቁራሽ እንጄራ ማሳደግ እንዳልቻለ ዛሬ አለም ሁሉ የተረዳዉ ይመስላል።ወያኔና ዕድገት ሆድና ጀርባ ናቸዉ። ስለሆነም እድገት፤ ፍትህ፤ እኩልነትና ሠላም የናፈቀን ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ያለን አማራጭ ወያኔን ማስወገድ ብቻ ነዉ።

የወያኔ አባላት እንኳን ዋሽተዉ ሰዉ ገድለዉም ቢሆን ተጠያቂነት የሚባል ነገር ስለማያዉቁ ፍርዳቸዉ የበቀል ንግግራቸዉ የጥላቻ ነዉ፤ ደግሞም መታወቂያ ካርዳቸዉ ዉሸት ነዉና ሲዋሹ ዉለዉ ሲዋሹ ቢያድሩ ቅርም የሚላቸዉ አይመስልም። እነዚህ ከሀዲዎች ሲመሽ የሚጨንቃቸዉ ነገ ምን እንዋሻለን የሚል ስጋት ነዉ እንጂ ትናንት የዋሹትዉሸት አይደለም። ለምሳሌ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ የግንቦቱ ምርጫ እለት ረፋዱ ላይ የሮይተር ጋዜጠኛ ምርጫዉን አስመልክቶ የጠየቀዉን ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ ብሎ ነበር – “ለሰባት አመታት ኤኮኖሚን በድርብ አኀዝ ያሳደገ ፓርቲ በምርጫ ሲሸነፍ በዓለም ታይቶ አይታወቅም”እዚህ ላይ መሠረታዊዉ ጥያቄ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል ወይም አላደገም የሚለዉ ጥያቄ አይደለም። ይህንንማጥያቄ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስራ አጥተዉ አረብ አገር ለባርነት የሚጋዙት እህቶቻችንና የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ የራሱን ሆድ በገመድ እያሰረ ልጆቹን በፈረቃ የሚመግበዉ አባወራ ሳይጠየቁ መልሰዉታል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ለሰባት አመታት በድርብ አኀዝ ያደገዉ ከመቼ አስከመቼ ነዉ?

መቼም መለስ ዜናዊ ሲዋሽ ለነገ የማይል ሰዉ ሆኖ ነዉ እንጂ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የኢትዮጵያን አርሶ አደርና ሠራተኛ ህዝብ በሚያረካ መልኩ ለአንዲት አመት እንኳን በስርአት ያደገዉ መቼ ነዉ? የአለም ባንክንና የመለስ ዜናዊን የራሱን ስታትሰቲክስ ጽህፈት ቤት ያለፉት አስር አመታት አመታዊ ሪፖርት ተመለከትንና አቶ መለስ ለዋሹት ዉሸት እኛ አፈርንላቸዉ እንጂ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚማ ህዝብን በሚጠቅም መልኩ እንኳን ሰባት አመት አንድም ቀን አድጎ አያዉቅም።

እዉነቱ ይዉጣ ከተባለ – በዚህ እንደ “ዬኔ ቢጤ” ዲሪቶ ከዚህም ከዚያም በህዝብ ስም በተሰበሰበ ገንዘብ በሚንቀሳቀሰዉ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የተጠቀመ የህብረተሰብ ክፍል ቢኖር የኤፎርት ባለቤት የሆነዉ የትግራይ ክልል፤ የወያኔ ባለስልጣኖች፤ ወያኔን የተጠጉ ጥቂት ሆዳሞችና የሼክ አላሙዲን ንብረት የሆነዉ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባኒያ ብቻ ናቸዉ። የተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እነዚህ የቀን ጅቦች እየበሉ ሲያገሱ ከመመልከት አልፎቤሳቤስቲን ደርሶት አያዉቅም። ባጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያዉስጥ እንሹራንስ፤ ባንክ፤መንገድና ህንፃ ኮንስትራክሺን፤የህዝብና የጭነት ማመላለሻ፤ የንግድ፤የእርሻና የእንዱስተሪ ተቋሞችን በባለቤትነት ይዘዉ የሐገሪቱን ጥሬ ሐብት የሚቦጠቡጡት እነዚሁ በዘረኞችና በጥቂት ሆዳሞች የተያዙ ኩባኒያዎች ናቸዉ። ለዚህ ነዉ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” እንደሚባለዉ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ነዉ በተባለ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበላ አጥቶ በችግር የሚጠበሰዉ። በነገራችን ላይ ዛሬ የኢትዮጵያ የእድገት ደረጃ መለስ ዜናዊ ዶላር ባስታቀፉት ቁጥር ጦር እየላከ ከሚያሰቃያትና ለ20 አመት ሙሉ መንግስት ከሌላት ከሶማሊያ አጅግየከፋ ነዉ።

ባለፈዉ ሳምንት ታትሞ የወጣዉ ፋይናንሻል ታይምስ የተባለ ተአማኒነት ያለዉ መጽሔት ኢትዮጵያ ዉስጥ አገዛዙ አለ የሚለዉ እጥፍ ድርብ የኤኮኖሚ ዕድገት ዕርዳታ ለጋሾችን ለማስደሰት ሆን ተብሎ የተቆለለ የቁጥር ክምር ስለመሆኑ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር የለም ብሏል። የህንን የአደባባይ ምስጢር ደግሞ ዋሾዉ መለስ ዜናዊም ቢሆን ቢለዉ ቢሰራዉ አልደበቅ ስላለዉ ለመጀመሪያ ግዜ በአደባባይ የኢህአዴግን የቁጥር ማሳደግ ችሎታ በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ አምኗል።

በያዝነዉ የነሐሴ ወር እጅግ ካስገረሙን ነገሮች አንዱ የመለስ ዜናዊን “እድገት” የሚሉት የወሬ ቱማታ “ ጉ . . . ድ” ብለን ሳንጨርስ – የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ “በተስፋ የተሞሉት ቀጣዮቹ አምስት አመታት ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ በተመጽዋጭነት ስሟ አይነሳም” ብለዉ የተረቱት ተረት ነዉ። አቶ ሶፊያንና ፓርቲያቸዉ እህአዴግ እናደርጋለን ብለዉ ለህዝብ ቃል ከገቡት ነገሮች ሲሶዉን ያክል እንኳን በተግባር የመተርጎም ችሎታ ቢኖራቸዉ ኖሮ የአቶ ሶፊያን መልካም ምኞት አለምን ሁሉ ያስደስት ነበር።በነገራችን ላይ አቶ ሶፊያንአስበዉ ይሆን አዳልጧቸዉ የዛሬ አምስት አመት የተናገሩትን ነገር እሳቸዉ ቢዘነጉትም ተስፋ የተገባለት የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የሚዘነጋዉ አይመስለንም። የ1997ቱ ምርጫ እንዳለቀ አቶ ሶፊያን “በ2015 ዓም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ጋር ትሰለፋለች” ብለዉን ነበር። የሚገርመዉ የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህንን ሲናገሩ ኢትዮጵያ በአለማችን ላይ ከታች ወደ ላይ 4ኛዋ ደሃ አገር ነበረች። ዛሬ ከአምስት የወያኔ የእድገት አመታት በኋላ ኢትዮጵያ ከሁለት የመጨረሻ ደሀ አገሮች ወስጥ አንዷ ናት።እያደገ ሄዶ መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ተርታ ያሰልፈናል ብለዉ አቶ ሶፊያን የተናገሩለት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ቁልቁል ወይም የኋሊዮሽ እያደገ አገራችንን ጭራሽ የመጨረሻዋ ደሃ አገር አሰኝቷታል። ሰሞኑን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከተመድ ጋር በመተባበር ባወጣዉ ሰፋ ያለ ጥናታዊ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ በድህነት ከታች ወደ ላይ ሁለተኛዋ አገር ሆናለች። ድህነታችንና ኋላ ቀርነታችን እጅግ የሚያንገበግበን ቢሆንም እዚህ ላይ ግን በጣም የሚያሳዝነን “ታዳጊዉ የአፍሪካ አኮኖሚ” የተባለለትን ፈጣን ኤኮኖሚ ይዘን ዛሬም ሩጫችን ወደፊት ሳይሆን ወደ ኋላ መሆኑ ነዉ።

መቼም መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ሲሰሩም ሲያወሩም ፀባያቸዉ ዛሬ የገነቡትን ነገ ማፍረስ ነዉ። እንግዲህ ይታያችሁ ማፍረስ – መገንባት ማፍረስ – መገንባት . . . ሃያ አመት ሙሉ! ከሰሞኑ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ተመፅወጭነት የሚባል ቋንቋ ከኢትዮጵያ ምድር ይወገዳል ብለዉን ነበር። የሚገርመዉ የአቶ ሶፊያን ንግግር ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ገና የታተመበት ቀለም ሳይደርቅ ነዉ መለስ ዜናዊ መጥቶ በቀጣዮቹ አምስት አመታት የተያዘዉ የልማትና ዕድገት ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ይፈፀማል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል የገለፀዉ። የማንን አምነን የማንን እንደምንተዉ ባናዉቅም እንደ መለስ ዜናዊ አባባል ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት አመታት በተመፅዋጭነት ትቀጥላለች ማለት ነዉ። እኛም አትልፉ ሲለን በአቶ ሶፊያን ልዩ ትዕዛዝ ከመዝገበ ቃላታችን ዉስጥ እንዲፋቅ ያሰመርንበት “ተመፅዋጭነት” የሚለዉ ቃል ለሌላ አምስት አመት ሊሰነብትልን ነዉ። ባጠቃላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ያለ የሌለ ብር ደምረዉ ልመና አበቃ ሲሉን ጠ/ሚኒስትሩ ግን እሳቸዉና ጋደኞቻቸዉ ኪስ የሚገባዉን የገንዘብ ልክ ያዉቃሉና ብር የለም ልመናዉ ይቀጥላል ብለዉናል።

በሌላ በኩል ደግሞ መለስ ዜናዊ ባለፈዉ ሐሙስ ለአገር ዉስጥ ጋዜጠኞች በሰጠዉ መግለጫ ገዢዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ኤኮኖሚዉ አደገ የሚለን ከቁጥር ጋር እየተጫወተ መሆኑን አምኖ ይህ የቁጥር ማሳደግ ጨዋታ ከዛሬ በኋላ አይደገምም ብሏል። ለሁሉም መለስ ዜናዊ እንደዚህ ነበር ያለዉ – “መንግስት አነስተኛ የልማት ዕቅድ ይዞ ዕቅዴን መቶ በመቶ አሟልቻለሁ ከሚል ይልቅ ቢያንስ በዕቅድና በሙከራ ደረጃ ትልቅ ነገር አስቦ በተግባር ቢንቀሳቀስ ይሻላል” ከዚህ የመለስ ዜናዊ አባባል የኢትዮጵያ ህዝብ ሚከተሉትን ሁለት ቁም ነገሮች ይረዳል ብለን እናምናለን። በመጀመሪያ አገዛዙ ትልቅ ነገር አስቦ እንደማይንቀሳቀስ ጠ/ሚኒስትር ተብዬዉ በግልፅ ተናግሯል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አገዛዙ <<የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ>> በእጥፍ ድርብ አደገ የሚለዉ ሆን ብሎ ቁጥሮችን በማሳደግ መሆኑን መለስ ዜናዊ በተዘዋዋሪ ግልፅ አድርጎታል።

አገራችን ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኃይለስላሴና በደርግ ዘመነ መንግስትም ቢሆን ደሃ አገር ነበረችና ዛሬ ኢትዮጵያ ደሃ ናት ሲባል ብዙ ላይገርመን ይችላል። ሀቁ ግን እንደዚህ ነዉ – ከ80 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ 90% ወይም 72 ሚሊዮኑ በከፍተኛ ድህነት ዉስጥ ነዉ የሚኖረዉ። 31 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ የቀን ወጪዉ ከ $1.25 ያነሰ ነዉ።49.6 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ በቂ የትምህርት ዕድል አያገኝም። እነዚህ መረጃዎች ደግሞ እኛ የሰራናቸዉ ሳይሆኑ የተ.መ. ድ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያጠናቀረዉ ጥናታዊ ዉጤት ነዉ።እዚህ ላይ ጭራሽ ሊገባን ያልቻለ ነገር ቢኖር አገራችን ይህን የመሰለ የድህነት ማጥ ዉስጥ የገባችዉ በአፍሪካ ዉስጥ ቁጥር አንድ የምግብና የገንዘብዕርዳታ ተቀባይ አገር ሆና ነዉ። አያምጣዉ እንጂ በአንድ አጋጣሚ ለጋሽ አገሮች እጃቸዉን ቢያጥፉ ምን ይዉጠን ይሆን?

በ2002ቱ ምርጫ ዋዜማና ማግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ጆሮ ካደነቆሩት የወያኔ ፕሮፓጋንዳዎች አንዱ “የኤኮኖሚ እድገት” የሚባል በእጅ የማይዳሰስ በአይን የማይታይ የዘረኞች ባዶ ጫጫታ ነበር። በትግራይ ተራድኦ (ኤፎርት) ስር የሚገኙትን የመንገድና የህንፃ ኮንስትራክሺን ድርጅቶች ለመጥቀም ሲባል በየቦታዉ የሚገተሩት ህንፃዎችና ተሰሩ የሚባሉት መንገዶች ሰዉ ሳይኖርባቸዉና መኪና ሳይሄድባቸዉ የጥገና እቅድ የሚወጣላቸዉ ጉዶች ናቸዉ። የሚገርመዉ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአስተማማኝ ክረምት ከበጋ የሚያገለግሉት መንገዶች፤ ድልድዮችና የመሬት ስር መተላለፊያዎች ጣሊያኖች የዛሬ ሰባ አመት የገነቧቸዉ ናቸዉ እንጂ የወያኔ ነካ ነካ መንገዶችና ህንፃዎችማ ሰኞና ማክሰኞ እየተገነቡ ሐሙስና አርብ ዕድሳት የሚያስፈልሃቸዉ የወያኔን ኪስ ለመሙላት ብቻ የሚሰሩ ስራዎች ናቸዉ።

በአገራችን በኢትዮጵያ ታሪክ በአጭር ግዜ ዉስጥ ከፍተኛ የግንባታ ስራ የተሰራበት ወቅት ቢኖር ከ1928 እስከ 1933 የነበሩት አምስት አመታት ናቸዉ። በእነዚህ አምስት አመታት ዉስጥ ጣሊያኖች እየወጉንም ቢሆን የወያኔ ዘረኞች በ20 አመት ከሰሩት ስራ እጅግ የሚበልጥ ስራ ሰርተዋል። ታድያ የኢትዮጵያ ህዝብ ለምን ጣሊያኖችን እጁን ዘርቶ አልተቀበላቸዉም? ከአገራችን ወጣ ብለን የደቡብ አፍሪካን ታሪክ ስንመለከት ደግሞ ከ1900- 1990 በነበሩት 90 አመታት ዉስጥ በቴክኖሎጂ፤በንግድ፤በእርሻ፤በእንዱስትሪና በወታደራዊ ጥንካሬ ደቡብ አፈሪካን የመሰለ ጠንካራ አገር አፍሪካ ዉስጥ አልነበረም። ደቡብ አፍሪካ የኑክለር ሀይል ባለቤት ነበረች፤ ደቡብ አፍሪካ በአለማችን የመጀመሪያዉ የልብ ቀዶ ጥገና የተካሄደባት አገር ናት። ታዲያ እንደዚህ አይነቷን ሀብታምና በእድገት የገፋች አገር ጥቁር አፍሪካዉያን አምርረዉ የታገሉት ለምንድነዉ? የእነዚህን ሁለት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ብዙ መጓዝ የሚያስፈልግ አይመስለንም። የጣሊያን ፋሺስቶችያሰኛቸዉን ያክል መንገድና ህንፃ ቢገነቡም የአባቶቻችን የነፃነት ፍላጎት በምንም ያክል ቁሳዊ ኃብት የሚገመት አልነበረምና የጣሊያን ወራሪዎችን አልተቀበሉም። ደቡብ አፍሪካ ዉስጥ ደግሞ ነጮቹ ጥቁሮችን በእኩልነት የማይመለከቱ ዘረኞች ስለነበሩ የደቡብ አፍሪካ ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት የጥቁር ደቡብ አፍሪካዉያንን የነፃነት ፍላጎት አልገታዉም። እንግዲህ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይእራሳቸዉን የጫኑት ወያኔዎች እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጮች ዘረኞች እንደ ጣሊያን ፋሺስቶች ወራሪዎች ናቸዉና የኢትዮጵያ ህዝብ በምንም አይነት ሊቀበላቸዉም ሆነ ሊታገሳቸዉ አይገባም።

ኢትዮጵያ በዕድገት ገስግሳ በአንድ ጀምበር የዛሬዋን አሜሪካ ብታስከነዳ እንኳን ነፃነት፤ፍትህና እኩልነት አገራችን ዉስጥ እስካልተረጋገጠ ድረስ ትግላችን ላፍታም ቢሆን መቆም የለበትም። ነፃነታችንን ገፍፈዉ ምግብና ቤት እየሰጡ ከሚደልሉን ነፃነታችንን ያክብሩልንና ያሰኘንን ምግብና ቤት እኛዉ እንሰራለን። የራበን ነፃነት ነዉ እንጂ ምግብ አይደለም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ መብቱንና ነፃነቱን ለድርድር አቅርቦ ወይም በኤኮኖሚ ጥቅም ለዉጦ አያዉቅም። ከመንግስት ተቀዳሚ ተግባሮች አንዱ ኤኮኖሚን ማሳደግና የህዝብን መሠረታዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነዉ። እንደዚህ ማለት ግን ኤኮኖሚን ያሳደገ ገዢ ፓርቲ ስልጣን እንደያዘ ዕድሜ ልኩን ይቆያል ማለት አይደለም። የወያኔ ዘረኞች አሳደግነዉ የሚሉት ኤኮኖሚ ደግሞ ታይቶ የማይዳሰስ ምትሀትቢበሉትየማይጠጋ መዐት ነዉ። መለስ ዜናዊ እድገትን በተመለከተ ያልተሰራ ስራ ተሰርቷል፤ ያልተጀመረ ነገር አልቋል እያለ በዋሸ ቁጥር የሚያምኑትን ፈረንጆች ቢያሞኝም – ሺ ዉሸት ቢከመር አንድ አዉነት አይወጣዉምና ዛሬ ሳይወድ በግድ ዉሎ ያደረ ዉሸቱን ማስተባበል ጀምሯል። ኮንዶሚኒየም በአስርሺዎች ተሰራ እየተባለ የበረንዳ አዳሪዉ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩና የእርሻ ምርት በእጥፍ አደገ እየተባለ የረሀብተኛዉ ቁጥር በፍጥነት ማደጉ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ ደልቶት የሚኖረዉ መለስ ዜናዊ “ወርቃማዉ” እያለ የሚጠራዉ ጥቂት የህብረተሰብ ክፍል ብቻ መሆኑን ዘረኛዉ መለስ ዜናዊን በአንቀልባ የተሸከሙት ምዕራባዉያን ወዳጆቹ ጭምር የተረዱት ይመስላል።አንዳንዶቻችን ወያኔን ከሚገባን በላይ ሰለለመድነዉ እንዳሳደግነዉ ዉሻ አብሮ መዝለል ይቃጣናል፤ አንዳንዶቻችን ደግሞ ወያኔ ቢከፋም ኢትዮጵያን ቀይሯታል የሚል ቅዠት ዉስጥ የገባን ይመስላል። ከእነዚህ ከሁለቱም ያልሆንነዉ ደግሞ እነ እገሌ ናቸዉ እንጂ አገር አጥፊዎች መለስ ዜናዊማ ምን አጠፋ “ይቀጥል” የሚለዉን የሠለሞን ተካልኝን ዘፈን የወደድነዉ ይመስላል። ይህንን ሌሎቹ ናቸዉ እንጂ መለስ ዜናዊማ ከዚህ በላይ ምን ያድርግየሚለዉን የነፈሰበትተረት ስንሰማ አንድ ቆየት ያለ ተረት ትዝ አለን – አንድ እንቅልፍ ባይናቸዉ አልዞርያለ ቄስ በጧት ተነስተዉ ከወዲህ ወዲያ ሲሉ – ገበሬዉ በሬዎቹን ፈትቶ ብሳና ስር ቁጭ ብሎ ዉኃ ሲጠጣ አዩትና ጠጋ ብለዉ – አያ እገሌ ብሳና ይሸታል እንዴ ብለዉ ይጠይቁታል። ገበሬዉ ከተቀመጠበት ተነሳና . . . ብሳና የሸታል! ዛፎቹን ሁሉ መሽተት ያሰተማራቸዉ ማን ሆነና ነዉ ብሎ መለሰላቸዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ዛሬ ጥያቄዉ ኤኮኖሚዉ አደገ ወይም አላደገም ወይም ከመለስ ዜናዊና ከስብሀት ነጋ ማን ይሻላል አይደለም። መለስና ስብሀት ምንም የሚመረጥ ነገር የላቸዉም። ሁለቱም መነቀል ያለባቸዉ ብሳናዎች ናቸዉ። እነዚህ ሁለት ሰዎች ወይም እነሱ የሚመሩት ህወሀት የሚባል ድርጅት ከአገራችን እስካልተነቀለ ድረስ ትንሽ ቆይቶ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንኳን ኤኮኖሚዉ ዛፍም አያድግም። ምርጫችን አንድ – አንድ ብቻ ነዉ። እሱም ነፃነት ነዉ። ነፃነት ደግሞ የብዙኋን ምርጫ ነዉና የሚረጋገጠዉበብዙኋን ትግል ነዉ።