የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀጥለውን ዓመት የድጎማ በጀት አፀደቀ

– ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል

ባለፈው እሑድ የተሰበሰበው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን የድጎማ በጀት ቀመር አፀደቀ፡፡


ምክር ቤቱ የድጎማ ቀመርና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት በአቶ ሽፈራው ሸጉጤ የቀረበውን የ2004 ዓ.ም. የክልሎች የድጎማ ቀመር ከተወያየበት በኋላ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

በእስካሁኑ ሒደት ግን የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሚቀጥለውን ዓመት የአገሪቱን በጀት አዘጋጅቶ አላጠናቀቀም፡፡ ሚኒስቴሩ በጀቱን አዘጋጅቶ ሲጨርስ ከአጠቃላዩ በጀት ውስጥ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስተቀር፣ የድሬዳዋ ከተማና ዘጠኙ ክልሎች ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀላቸው ቀመር መሠረት የድጎማ በጀቱን ይከፋፈላሉ፡፡

በቀመሩ ቅልቁን ድርሻ የሚይዙት በቅደም ተከተል የመጀመሪያው ኦሮሚያ 32.53 በመቶ፣ አማራ 23.33 በመቶ፣ ደቡብ ክልል 19.90 በመቶ፣ ሶማሌ 8.34 በመቶ፣ ትግራይ 7.04 በመቶ፣ አፋር 3.34 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 1.96 በመቶ፣ ጋምቤላ 1.57 በመቶ፣ ድሬዳዋ 1.01 በመቶ ናቸው፡፡ ከበጀቱ ዝቅተኛው ተጠቃሚ ሐረሪ ክልል ሲሆን፣ የሚደርሰውም 0.89 በመቶ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፓርቲ መስራች የሆኑት አራቱ ትላልቅ ክልሎች በፈቃደኝነት የአጠቃላይ በጀቱን አንድ በመቶ ታዳጊ ለሚባሉት ክልሎችና ለድሬዳዋ ከተማ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

የድጎማ በጀቱ ቀመር የተዘጋጀው በሁለት መሠረታዊ መመዘኛዎች ነው፡፡ የመጀመርያው በክልሎቹ የወጭ ፍላጐት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ገቢ በመሰብሰብ አቅማቸው መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአቶ ካሣ ተክለ ብርሃን የሚመራው በፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2005 ዓ.ም. ለክልሎች በምን ዓይነት መንገዶች የድጎማ በጀቱ ይከፋፈል የሚለውን ከወዲሁ ማጥናት መጀመሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዚህ ጥናት ውስጥ የየክልሎቹ የፋይናንስና የገቢ መሥርያ ቤቶች፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተካተቱ ሲሆን፣ የፌዴሬሽኑ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጥናት ዳይሬክቶሬት ለሁሉም ክልሎች የመሠረተ ልማት ተቋማት መጠይቅ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

የድጎማ በጀት ቀመር በፌዴሬሸን ምክር ቤት ውስጥ በአወዛጋቢነቱ ይታወቃል፡፡ በዕድገት ወደኋላ የቀሩ ክልሎች የሚባሉት ከክልላቸው የቆዳ ስፋት፣ ከሕዝባቸው ተበታትኖ መኖር፣ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰፊ የድንበር ክልል ያላቸው ከመሆኑና ከፀጥታ ማስጠበቅ አንፃር የሚመደብላቸው ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነ በመግለጽ ቀመሩን ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡

ይህንን ቅሬታ በተወሰነ ሁኔታ ለማስወገድ አራቱ ትላልቅ ክልሎች ከድጎማ በጀቱ ላይ አንድ በመቶ በመቀነስ ለእነዚህ ክልሎች እንዲከፋፈል በፈቃደኝነት መለገሳቸው ታውቋል፡፡  

በውድነህ ዘነበ