የኤርትራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የተቃውሞ ሠልፍ ጠሩ
በየማነ ናግሽ | ሪፖርተር
በመጪው ዓመት መጀመሪያ ወራት የኤርትራ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ለማካሄድና ከአገር ውጭ ብሔራዊ ሸንጐ ለመመስረት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ብሔራዊ ኮሚሽን፣ የኤርትራ ነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በመጪው ግንቦት ዓለም አቀፍ ሠልፍ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ ከተመሠረተ ስድስት ወር የሆነውና በመጪው ጥቅምት ወር አካባቢ የኤርትራ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ለማካሄድ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው 53 አባላት ያቀፈው ብሔራዊ ኮሚሽን፣ ከመጋቢት 6 እስከ 12 ቀን 2003 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ገነት ሆቴል ባካሄደው ሁለተኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ የእስካሁን እንቅስቃሴውን የገመገመ ሲሆን፣ በኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታዎችም ላይ መነጋገሩ ታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተወልደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤርትራ ወታደሮች በድሃ ዜጐች ላይ ማነጣጠሩን ትተው በመንግሥት ላይ እንዲያምጹ ኮሚሽኑ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ግንቦት 16 ቀን 2003 ዓ.ም. በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኤርትራውያን የተቃውሞ ሠልፍ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚሉት፣ ኤርትራን ጨምሮ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በአውስትራሊያ በሚገኙ ኤርትራውያን ዲያስፖራ በብዛት የሚገኙባቸው ትላልቅ ከተሞች በኤርትራ መንግሥት ላይ የተቃውሞ ሠልፍ ተጠርቷል፡፡
ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ በኤርትራ መንግሥት ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ ማለቱን ማድነቁን ገልጾ፣ ጉዳዩን በቀዳሚነት የሚመለከተው የኤርትራ ሕዝብና ወታደር ደግሞ በያለበት ሆኖ ፀረ የኢሳያስ መንግሥት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡