የሸራተን አዲስ ውዝግብ ቀጥሏል
በዘካሪያስ ስንታየሁ | ሪፖርተር
በሸራተን አዲስ ሆቴል የተፈጠረው ውዝግብ ባለፈው ረቡዕ እልባት ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ እስካሁን መፍትሔ ማግኘት አልቻለም፡፡ ሆኖም ችግሩን ለመፍታት በሆቴሉ ማኔጅመንትና በሠራተኛ ማኅበሩ መካከል የተጀመረው ድርድር መቀጠሉን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሆቴሉ ማኔጅመንት ባለፈው ማክሰኞ የሆቴሉን ሠራተኞች በሙሉ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በላሊበላ አዳራሽ ሰብስቦ ያነጋገረ ሲሆን፣ ሠራተኞቹ በአንድነት የሠራተኛ ማኅበሩ ድምፅ እንዲሰማላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ አብነት ገብረ መስቀልና የሆቴሉ የሰው ኃይል አስተዳደር አቶ ዳንኤል መዝገቡ 600 አካባቢ የሚሆኑ የሆቴሉ ሠራተኞችን ሰብስበው ያወያዩ ሲሆን፣ አስተያየታቸውን የሰጡ አብዛኞቹ ሠራተኞች ማኔጅመንቱ ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር ተደራድሮ ችግሩን እንዲፈታው ጠይቀዋል፡፡ አቶ አብነትም ማኔጅመንቱ ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር ተወያይተው በነጋታው ውጤቱን እንደሚያስታውቁ ገልጸው፣ ሠራተኞቹ አዳራሹን ለቀው ከወጡ በኋላ ማኔጅመንቱ ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር ድርድሩን መቀጠሉ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
አቶ አብነት ሆቴሉ ሪዘርቬሽን መቀበል ያቆመበትንም ምክንያት ሲያስረዱ፣ የሆቴሉ ባለቤት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን የተፈጠረው ውዝግብ እልባት እስኪያገኝ ድረስ እንዲቆም በማዘዛቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ አብነት በስብሰባው የተገኙት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ባለቤቱ ወክለው ስለላኳቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ አቶ አብነት ረቡዕ ውጤቱን ለሠራተኛው እንደሚገልጹ ተናግረውም ነበር፡፡
ረቡዕ ከሰዓት ላይ የሆቴሉ ሠራተኞችን በሙሉ ማኔጅመንቱና የሠራተኛ ማኅበሩ የሰበሰቧቸው ሲሆን፣ ችግሩን ለመፍታት ማኔጅመንቱና የሠራተኛ ማኅበሩ ድርድራቸውን እንደሚቀጥሉ ተነግሯቸዋል፡፡ ሆኖም ከድርድሩ መቀጠል ውጪ መፍትሔ ላይ አለመደረሱ ታውቋል፡፡ ሠራተኞቹም ሥራቸውን መቀጠል እንደሚገባቸው በስብሰባው ወቅት ተነግሯቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፉጂ ደሴት ዜግነት ያላቸው የሆቴሉ የምግብና የመጠጥ ክፍል ምክትል ኃላፊ ጄ ራም ከሥራ መባረራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ምክትል ኃላፊው አንዳንድ የሆቴሉ ሠራተኞች መጥፎ የሰውነት ጠረን አላቸው፤ በመሆኑም ንጽህናቸውን ይጠብቁ የሚል መልዕክት ለክፍል ኃላፊዎች በኢሜል አሰራጭተው ነበር፡፡ በሁኔታው የተበሳጩ ሠራተኞችም ለማኔጅመንቱ ቅሬታቸውን ያስገቡ ቢሆንም፣ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ዦን ፒር ማኒጐፍ በግለሰቡ ላይ የራሴን ዕርምጃ እወስዳለሁ እንጂ ከሥራ አላባርራቸውም የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ምንጮቹ አስታውሰዋል፡፡
የሆቴሉ ማኔጅመንት ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. አስተላልፎት የነበረውና ከየካቲት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሆቴሉ ሪዘርቬሽን እንዲያቆም የሚለው ትዕዛዝ ተሽሮ ከየካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሪዘርቬሽን ተጀምሯል፡፡
ከየካቲት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሆቴሉ እንደሚዘጋ ማኔጅመንቱ አስታውቆ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡