ስዬ አብርሃ መኖሪያ ቤቱን እንዲለቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው
በታምሩ ጽጌ | ሪፖርተር
የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትርና የመድረክ ከፍተኛ አመራር አቶ ስዬ አብርሃ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራይተውት የሚኖሩበትን ቤት ከጥር 30 ቀን 2003 ዓ.ም. በፊት እንዲያስረክቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡ ጥር 6 ቀን 2003 ዓ.ም. የቤት ኪራይ ከፍለው ሲመለሱ በመኖሪያ ቤታቸው አጥር ላይ ማስጠንቀቂያው ተለጥፎ ማየታቸውን የገለጹት አቶ ስዬ፣ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሕጋዊ በሆነ ውል ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ተፈራርመው የተከራዩትንና እየኖሩበት የሚገኝ ቤትን ያለምንም ማስጠንቀቂያ ‹‹በሦስት ቀናት ውስጥ እንድትለቅ›› የሚል ማስጠንቀቂያ ተለጥፎ በማየታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በቁጥር 503/ሰቅ/ በ140/17/19/106 ጥር 6 ቀን 2003 ዓ.ም. የጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፤ ቤቱ ከአዋጅ ውጭ የተወረሰ መሆኑ ተረጋግጦ ለባለቤቶቹ መመለስ እንዳለበት ፍርድ ቤት ለፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እንደጻፈለት እንደሚጠቁም አቶ ስዬ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የፍርድ ባለ መብቶች የፍርድ አፈጻጸም በመክፈታቸውና ለጥር 9 ቀን 2003 ዓ.ም. የተቀጠረ በመሆኑ ከቀነ ቀጠሮው በፊት ጥር 8 ቀን 2003 ዓ.ም. የመኖሪያ ቤታቸውን ቁልፍ ለኤጀንሲው እንዲያስረክቡ ማስጠንቀቂያው እንደሚያስረዳ አቶ ስዬ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤት ቤቱ ከአዋጅ ውጭ የተወረሰ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲመለስላቸው የተባሉት የአቶ ደረጀ ደሬሳ ወራሽ ወ/ሮ ገነት ፍስሀ መሆናቸውንም በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ላይ እንደተገለጸ ተናግረዋል፡፡
ምንም የሚያውቁት ነገር ስላልነበራቸው ‹‹እንዴት እንደዚህ ይሆናል›› በሚል የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲን ቢያነጋግሩም፣ ‹‹ይኼ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ የፍርድ ቤት ውሳኔ ስለሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አቶ ስዬ ገልጸዋል፡፡
‹‹ሕፃናት ልጆች አሉኝ፤ ቤተሰብ አለኝ፤ ቤቱ ሕግን ተከትሎ ለባለቤቶቹ የሚመለስ ከሆነ ለእኔ ተለዋጭ ቤት ሊሰጠኝ ይገባል፤›› የሚሉት አቶ ስዬ፣ ቤቱ ለባለቤቶቹ በመመለሱ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንደሌላቸው፤ ነገር ግን እሳቸውም ዜጋ በመሆናቸው መብታቸው ሊጠበቅላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት መንግሥት ለባለሥልጣናት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ሲሰጥ ‹‹አልፈልግም›› በማለታቸው ቤትም ሆነ መሬት እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ስዬ፤ አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ ቤት ተከራይቶ መኖር አስቸጋሪ በመሆኑ የሚመለከተው አካል (ኤጀንሲው) ልዋጭ ቤት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ስዬ እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበትን ቤት ከ1991 ዓ.ም. ጀምረው እየኖሩበት ሲሆን፤ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ (በእስር ላይ እያሉ) ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ውል በመፈጸም በወር 1100.00 ብር እየከፈሉ ይኖሩበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ተለዋጭ ቤት ሳይሰጣቸው፣ በአጭር ቀናት ውስጥ ለምን እንዲለቁ እንደተደረገ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የደንበኞች አገልግሎት ቡድን መሪና ውል አፅዳቂ የሆኑትን ወ/ሮ አለምነሽ ወልዴን አነጋግረናቸው፣ ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነና በኤጀንሲው መመሪያ መሠረት በሕግ እንዲለቁ ለሚደረጉ ተከራዮች ልዋጭ ቤት እንዳማይሰጡ ገልጸዋል፡፡
‹‹አቶ ስዬ እንዲለቁ ያደረግነው እኛ ሳንሆን፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ባጭር ቀናት እንድናስለቅቅ ደብዳቤ ስለጻፈልን ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ አለምነሽ፤ በሦስት ቀናት ውስጥ ልቀቁ ያሉት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑን ጭምር ስለገለጹላቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ኤጀንሲው ካከራየው ደንበኛ ጋር ውሉን ካላቋረጠ ፍርድ ቤቱ ቅጣት እንደሚጥልበት የሚናገሩት ወ/ሮ አለምነሽ፣ ጊዜው አጭር መሆኑን በመግለጽና ጊዜ እንዲሰጣቸው በጠበቃቸው በኩል ፍርድ ቤቱን በመጠየቃቸው እስከ ጥር 30 ቀን 2003 ዓ.ም. ጊዜ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡