ዱባይ ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ የአሠሪዋን ብልት ቆረጠች

(ሪፖርተር) — ዱባይ ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሠራተኛ የአሠሪዋን ብልት በመቁረጧ ምክንያት በቁጥጥር ሥር መዋሏን ኤማራት አል ዮም ዘግቧል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የሰባ ዓመቱ አዛውንት ሁኔታውን ለፖሊስ ያስታወቁት ሰኞ ጧት ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊቷም ድርጊቱን ለመፈጸሟ የእምነት ቃሏን ሰጥታለች፡፡ ‹‹በሰውዬው በሚፈጽምብኝ ማስፈራራት ተሰላችቻለሁ፤›› ነበር ያለችው፡፡

ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሠራተኛ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ድርጊቱን ልትፈጽም የቻለችው አዛውንቱ ዘወትር ወሲባዊ ትንኮሳ ስለሚፈጽሙባት መሆኑን ገልጻለች፡፡

ድርጊቱ በተፈጸመበት ሰኞ ጧትም አዛውንቱ ማሳጅ እንድታደርጋቸው እንደጠየቋት፣ በዚህ ጥያቄያቸው በመናደድ በቢላ ብልታቸውን እንደቆረጠች ዘገባው ያመለክታል፡፡

በዘገባው ከባህረ ሰላጤው አገሮች የአንዱ ዜጋ እንደሆኑ የተጠቀሱት አዛውንት፣ ወደ ሆስፒታል ተወስደው የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡

የዱባይ ፖሊስ እንዳስታወቀው፣ ባለፈው ዓመት ዱባይ ውስጥ 665 ወንጀሎች በቤት ሠራተኞች ተጽመዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 305 የሚሆኑት ከአሠሪዎቻቸው ተደብቀው በመጥፋት፣ 113 በአስገድዶ መድፈር፣ 85 ሕገወጥ የመኖርያ ፈቃድ በመያዝ፣ 68 በእምነት ማጉደልና ስርቆት ይገኙበታል፡፡